የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገ ነው - ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገ ነው - ተጠቃሚዎች
አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት መርሃግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገ መምጣቱን በአርባ ምንጭ ከተማ የመርሃ-ግብሩ ተጠቃሚዎች ገለጹ።
በአርባ ምንጭ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመርሃ-ግብሩ ተጠቃሚዎች መርሀግብሩ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ጥሪት ለማፍራት እንዳገዛቸው ነው የገለጹት።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የ"እስታኒያ ዶሮ እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ ወጣት አዲስዓለም ደሴ ማህበሩ በ200ሺህ ብር ካፒታል 180 የሥጋና የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሳለች።
በአምስት አባላት ሥራውን የጀመረው ማህበሩ፣ የዕንቁላልና የሥጋ ዶሮዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ በገበያ ማረጋጋት ሥራው የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግራለች።
መንግስት የእርባታ ቦታ ከማመቻቸት በተጨማሪ በየጊዜው ሙያዊ ድጋፍ ማድረጉ ማህበሩ ውጤታማ እንዲሆን አግዟል።
በዚህም የማህበሩ ካፒታል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ700ሺህ በላይ መድረሱን ጠቅሳ፣ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የህብረተሰቡን የአመጋገብ ዘይቤ እየቀየረ መምጣቱንም ገልጻለች።
የ"ቤተሰብ እንስሳት እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ ቃለአብ ዳኛቸው በበኩሉ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለመውጣት አስችሎናል ብሏል።
ሥራቸውን ከአራት ዓመት በፊት በቀን 6 ሊትር ወተት በሚሰጡ አምስት የአካባቢው ዝርያ ላሞች እንደጀመሩ ገልጾ፣ በሂደት ሙሉ ለሙሉ በተሻሻሉ የላም ዝርያዎች በመተካት ምርታማነታቸውን መሳደጋቸውን ተናግሯል።
በዚህም ካፒታላቸው እያደገ መምጣቱንና ለሰባት ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ያመለከተው ወጣቱ፣ የወተት ምርታቸውን ለአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች እያቀረቡ መሆናቸውን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የወተት ላሞች ቁጥር 15 መድረሱን ገልጾ በየዕለቱ ከእያንዳንዳቸው 30 ሊትርና ከዚያ በላይ የወተት ምርት እንደሚያገኙ ጠቁሟል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ግብርና መምሪያ ሃላፊ መተኪያ አበበ የሌማት ትሩፋት የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል መርሀ ግብር መሆኑን አንስተዋል።
በመርሃ ግብሩ የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማጠናከርና የቤተሰብ ገቢን በማሻሻል በኩል ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፣ በተለይ በሕጻናትና በእናቶች ይስተዋሉ የነበሩ የሥነ ምግብ ችግሮችን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በከተማው የዶሮ፣ የንብ፣ የዓሣ፣ የወተት እና የሥጋ መንደሮች የተቋቋሙ ሲሆን፣ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችም ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።