ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የመድኃኒት አቅርቦትን በማሻሻል የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቷል

ነቀምቴ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የመድኃኒት አቅርቦትን በማሻሻል የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከአራቱ የወለጋ ዞኖች እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ባለድርሻ አካላት ጋር በመድኃኒት አቅርቦት ዙሪያ በነቀምቴ ከተማ ተወያይቷል።

በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ቱጁባ አዲኖ እንደገለጹት፤ የመድኃኒት አቅርቦትን በማሻሻልና የጤና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በኩል የዲጂታል አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ይህም በየጤና ተቋማቱ ያለውን የመድኃኒት ፍላጎት፣ ክምችት እና አቅርቦት በአግባቡ በመለየት አቅርቦቱን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ቢሮው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን ይበልጥ ለማሳለጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የነቀምቴ ቅርንጫፍ ኃላፊ ገመቹ ፍቅሩ በበኩላቸው፤ አስፈላጊ መድኃኒቶች በአግባቡ እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ብቸኛ አቅራቢ በመሆን ወሳኝ መድኃኒቶችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ድርጅቱ በክልሉ በሚገኙ 268 የጤና ጣቢያዎች እና 23 ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የደንቢዶሎ ሆስፒታል ተወካይ አዲሱ አቶምሳ በበኩላቸው፤ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመድኃኒት ግዥ በማከናወን ለአካባቢው ነዋሪዎች ማቅረብ መቻሉንና ይህም ለሕብረተሰቡ ትልቅ እፎይታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የሻንቡ ሆስፒታል የመድኃኒት አቅርቦት ክፍል ባለሙያ ቢሊሱማ ተፈራ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ የሕብረተሰቡን መድኃኒት ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም