ቀጥታ፡

በክልሉ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ስኬታማ ለማድረግ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ይጠናከራሉ

ጋምቤላ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ስኬታማ ለማድረግ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ይጠናከራሉ ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡን በማስመልከት የዕውቅና መርሃ ግብር ዛሬ በአኙዋሃ ዞን አቦቦ ወረዳ ተካሂዷል።




ርዕሰ መስተዳድሯ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እውን ለማድረግ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ይጠናከራሉ።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።

በተለይም በአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር በተከናወኑ ስራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ የተፈጥሮ ሚዛን በማስጠበቅበኩል ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ነባር የተፈጥሮ የደንና የብዝሃ ህይወት ሀብትን በመጠበቅ ለዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲውል በማድረግም አበረታች ስኬተቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።




ለዚህም ዋነኛ ማሳያው እውቅና የተሰጠው የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ ጨምሮ የማጃንግ የተፈጥሮ ደን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በሁለቱ ዞኖች በባዮስፌር ሪዘርቭነት የተመዘገቡት ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች የአየር ንብረት ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ልማት የላቀ አብርክቶ ያላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም የደን ሀብቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለዘላቂ ልማት ለመዋል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደሯ አስገንዝበዋል።




የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ አበራ ስዩም በበኩላቸው የአኙዋሃ ጥብቅ ደን በባዮስፌር ሪዘርቭ መመዝገቡ ኢትዮጵያ ለብዝሃ ህይወት ሀብት ጥበቃ ያላትን ቁጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዞኑ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገበው ጥብቅ ደን የተፈጥሮ ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን መገንበት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።




የመልካ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክትር ሰለሞን ከበደ እንዳሉት የአኙዋሃ ጥብቅ ደን በባዮስፌር ሪዘርቭነት በዩኔስኮ ሊመዘገብ የቻለው በውስጡ በያዛቸው እምቅ የእንስሳትና የዕፅዋት ብዝሃ ህይወት ሀብቶች ነው ብለዋል።

የተመዘገበው ጥብቅ ደን ለሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።




በዞኑ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመገበው ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ኢኮሚኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአኙዋሃ ዞን አስተዳደሪ አቶ ኝኬው ጊሎ ናቸው።

የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ በዩኔስኮ የተመዘገበ ሲሆን በውስጡ ከአንድ ሺህ በላይ የዕፅዋት፣ 327 የአእዋፍ፣ 69 የአጥቢና 17 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎችን እንደያዘ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም