ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ ልማት አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትና መሠረት እየሆነ ነው

ጭሮ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ ልማት አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትና መሠረት እየሆነን ነው ሲሉ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በዘርፉ ልማት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በምዕራብ ሐረርጌ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ከ396 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት ለተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ ችግኞች ተተክለው ለስኬት በቅተው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች በአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አርሶ አደር ዘሪሁን ከበደ እና አርሶ አደር መልካሙ ተስፋዬ፣ በአረንጓዴ አሻራ በየዓመቱ የተከሏቸው ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎችን ከመሸፈን ባለፈ የገቢ እና የምግብ ምንጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መትከል ከጀመሩ ወዲህ የመሬት ለምነትና እርጥበት እንዲጠበቅ ማስቻሉን አንስተው፤ በፍራፍሬ ልማት የተተከሉ ችግኞችም ጥቅም እየሰጡ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ ልማት አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትና መሠረት እየሆነን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ዋሴ በቀለ፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች በብዙ መልኩ ጥቅም እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።

አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትና መሠረት እና ጥሩ የገቢ ምንጭም እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ዘንድሮም ለችግኝ ተከላው የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን አንስተው፣ በመርሐ ግብሩ ከ396 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለችግኝ ተከላውም ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ዝግጁ መሆኑን አንስተው፣ ዕቅዱን ለማሳካት የሁላችንም ዝግጁነት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

የዞኑ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ተወካይ አቶ ፍጹም አማረ፤ በዞኑ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያም የታየው ተሳትፎ የልማት ሥራውን ለውጤት አብቅቶታል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የደን ሀብት መጠንን ከመጨመር ባለፈ፣ ለምግብ ዋስትና መሠረት እያኖረ እና አይነተኛ የሥራ ዕድልም ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም