የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
ባህርዳር፤ ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፦ የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
''ባህር ዳርን ወደ ላቀ ከፋታ ለመውሰድ የወጣቶች ሚና የማይተካ ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ ከወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ወጣቱ የዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ የጎላ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት የወጣቱ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም በባህር ዳር ከተማ ሰፋፊ የልማት ስራዎች በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ የወጣቱ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚነት የበለጠ ይጠናከራል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ ከተማውን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከል ማድረግ ያስቻሉ ውጤታማ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ለልማት ስራዎች ውጤታማነት ወጣቶች የከተማዋን ሰላም በማረጋገጥ አይተኬ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቱ የሰላም ባለቤትነቱን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማረጋገጡን አንስተው፤ በከተማው ዘላቂ ሰላምና ልማት የማስቀጠል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
በመድረኩ የከተማው ወጣቶች እየተሳተፉ ሲሆን በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።