የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ለመከላከል የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅሙን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ለመከላከል የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅሙን እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም እያሳደገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ሃይማኖት ዘለቀ ገለጹ።
ትውልዱ በጤናማ አስተሳሰብ ለአገር ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግና የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማስቻል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ስማርት ፎን የያዘ እያንዳንዱ ዜጋ የሚሳተፍበት ሰፊ የተግባቦት ዘዴ ተፈጥሯል።
ይህ አዝማሚያ ጥሩ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን አመልክተው፤ በሌላ በኩል ግን ሙያዊ ሥነ-ምግባር የሌላቸው በርካታ አካላት የሚሳተፉበት በመሆኑ ትልቅ ፈተና እየደቀነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
አብዛኛው የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥልጠና የሌለው በመሆኑ እንደ ትክክለኛነት፣ ሚዛናዊነት እና ታማኝነት ያሉ መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ምሰሶዎች አደጋ ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።
ይህም ኃላፊነት የማይወስዱ፣ ስህተታቸውን ሳያርሙ የሚያሰራጩ የይዘት ፈጣሪዎች መበራከታቸውን ጠቅሰው፤ የሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች ስርጭት እንዲሰፋ ምክንያት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ትውልዱ በጤናማ አስተሳሰብ ለአገር ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግና የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማስቻል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አገር አጥፊ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይህንን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም በጋራና በኃላፊነት ስሜት ሊረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመከላከል አሠራሩን ከማኑዋል ወደ ዲጂታል እየቀየረ መሆኑን ገልጸው፤ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ተቋሙን የማዘመን ሥራዎች በስፋት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት የተመዘገቡትንም ሆነ ያልተመዘገቡትን የዲጂታል ሚዲያ ይዘቶች በቴክኖሎጂ ለመከታተል የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል።
በተለይም የሰዎችን ድምፅና ምስል በመቀየርና በማስመሰል ሕዝብን ወደተሳሳተ ውሳኔ የሚመሩ የ"ዲፕ ፌክ" (Deepfake) ቴክኖሎጂዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ አጠናቆ ተቋሙ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ መሸጋገሩን ይፋ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ ፈቃድ የሰጣቸውን 73 የበይነ-መረብ ሚዲያዎችን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደፊትም ሁሉም የዲጂታል ሚዲያ አካላት ተመዝግበውና ኃላፊነት ወስደው እንዲሠሩ የሚያስገድድ የሕግ ማዕቀፍና የአዋጅ ማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም የሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ጥቆማዎች በ9192 ነጻ የስልክ መስመር ብቻ ይሰበሰቡ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ አሁን ግን "ኤማ አፕ" (Ema App) የተሰኘ አዲስ አፕሊኬሽን በይፋ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ይህ አሠራር በተዘረጋ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ47 በላይ ጥቆማዎች በዚሁ መተግበሪያ በኩል መድረሳቸውን ጠቅሰው፤ ሊንክና ስክሪንሹት መኖሩ የመረጃውን ባለቤት በቀላሉ ለማወቅና ተጠያቂነትን ለማስፈን ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የሐሰተኛ መረጃንና የጥላቻ ንግግርን የመከላከል ሥራ የባለሥልጣኑ ብቻ እንዳልሆነና ወደፊትም ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ከሌሎች የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ በማጠናከር እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።