ቀጥታ፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአዳዲስ ከተሞች የሚተገበረውን የ'’ብቃት'’ የወጣቶች የሥራ ልምምድ እና የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በአዳዲስ ከተሞች የሚተገበር የ'’ብቃት'’ የወጣቶች የሥራ ልምምድ እና የሥራ ማዕከላት አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡

ፕሮግራሙ ከዚህ ቀደም በ11 ከተሞች ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ዛሬ ይፋ በሆነው ፕሮግራም 16 ተጨማሪ ከተሞች የተካተቱ ሲሆን በዚህም 100ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለሁለት ዓመት የሚቆየው ይህ መርሐ ግብር የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ስትራቴጂያዊ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተመልክቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰሎሞን ሶካ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ መንግሥት የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።


 

በተለይ ከለውጡ ወዲህ በርካታ ዜጎች በተለያየ የሥራ መስክ ተሰማርተው ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም የወጣቶችን የሥራ ዕድል አማራጭ ለማስፋት በመደበኛነት ከሚከናወኑ ተግባራት በተጨማሪ፣ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር "ብቃት" የተሰኘውን የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ፕሮግራሙ በከተሞች የሚኖሩ ወጣቶችን በተለያዩ ተቋማት በማሰማራት የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ወጣቶቹ በቆይታቸው ከሚያገኙት የተግባር ዕውቀት ባሻገር የሥራ ልምድ እንዲያገኙ በማስቻል በቀላሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ-ግብር በቀጣይ በሚከናወነው የማስፋፊያ ሥራ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 የሆኑ ሴቶችንና ወጣቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም