የኢትዮጵያ ነፃ የጤና ትምህርት ዕድል በአፍሪካ የሕክምና ዲፕሎማሲ ሚናዋን እንድትወጣ እያስቻላት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ነፃ የጤና ትምህርት ዕድል በአፍሪካ የሕክምና ዲፕሎማሲ ሚናዋን እንድትወጣ እያስቻላት ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ተማሪዎች የምትሰጠው ነፃ የጤና ትምህርት ዕድል፣ ሀገሪቱ ድንበር የለሽ የሕክምና ዲፕሎማሲ ሚናዋን በብቃት እንድትወጣ እያደረጋት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።
በጤና ሚኒስቴር የነጻ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ያሉ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ እና የሌሎች ጎረቤት ሀገራት የጤና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የጤና ዘርፍ አገልግሎቶችን፣ የጤና ተቋማትን እና የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው።
የጤና ባለሙያዎቹ በኢትዮጵያ የጤና ትምህርት በሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፤ ከጎበኟቸው ተቋማት መካከል የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት አንዱ ነው።
የዚህ ጉብኝት ዋና ዓላማም ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ተጨባጭ ስራና ያላትን አቅም ለሰልጣኞቹ ማሳየት መሆኑ ተመልክቷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከ400 በላይ ለሚሆኑ በጤናው ዘርፍ ነፃ የጤና ትምህርት ዕድል በመስጠት እያስተማረች ትገኛለች።
ጤና ድንበር የለውም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የባለሙያዎቹ ጉብኝት በጤናው ዘርፍ በጋራ ለመስራት አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለአፍሪካ ሀገራት የምትሰጠው የነጻ ትምህርት ዕድል ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ እንደ ሀገርም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ነፃ የጤና ትምህርት ዕድሉ ድንበር የለሽ የሕክምና ዲፕሎማሲ ሚናዋን እንድትወጣ እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።