ኢትዮጵያውያን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተረጋጋ ፖለቲካና ለዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ተነሳሽነት በተግባር አሳይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተረጋጋ ፖለቲካና ለዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ተነሳሽነት በተግባር አሳይተዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በነቂስ በመሳተፍ ለተረጋጋ ፖለቲካና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለውን ተነሳሽነት በተግባር ማሳየቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ፡፡
ከ54 ሚሊየን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ የወሰዱበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ድምጽ መሰጠቱና ምርጫ መካሄዱ ይታወቃል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት፤ ዜጎች ከቅድመ ምርጫ እስከ ድምጽ መስጫው ዕለት ያሳዩት የነቃ ተሳትፎ የመንግስት ስልጣን መያዝ የሚገባው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ያሳየና ትምህርት የሰጠ ነው።
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተቋማት ልማትና አስተዳደር ተመራማሪው ዳንኤል አመንቴ (ዶ/ር)፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ በድምጽ አሰጣጡ ዕለት በነቂስ በመውጣት ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በነጻነት የመረጠበት ታሪካዊ ምርጫ መሆኑን አንስተዋል።
አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ጠንካራ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት፣ ዜጎች ምርጫን ለዴሞክራሲ ሥርዓት መዳበር ሁነኛ መሠረት መሆኑን በአግባቡ እንደተገነዘቡ ያስመሰከሩበት እንደሆነም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም እና አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጂማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የምርጫው ሂደት የሃሳብና የፖሊሲ ልዩነቶችን በሕዝብ ድምጽ የመወሰን የዴሞክራሲ ባህል ልምምድ እያደገ መምጣቱን ያሳየ ነው ብለዋል።
የሀገር ህልውና እና ልማት ቀጣይነት የሚረጋገጠው የዴሞክራሲ ተቋማት ሲጠናከሩ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ይበልጥ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር የሁሉም እገዛና ተሳትፎ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለምርጫው ሂደት ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ያደረጉት አበርክቶ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካና የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ዜጎች ያላቸውን ተነሳሽነት በተግባር ያሳዩበት ነው ብለዋል፡፡