ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ቀዳሚ ተመራጭ ከተማ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በስፋት የሚስተናገዱባት ቀዳሚ ተመራጭ መሆን መቻሏን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረትና ባከናወናቸው ግዙፍ የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታዎች ተመራጭ የስፖርት ማዕከል መሆን መቻሏን አመልክቷል።

ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተገነቡት ከ1,580 በላይ የሕዝብና የወጣቶች ስፖርት ማዕከላት ማኅበረሰባዊ ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ትልቅ መሠረት መሆኑን ገልጿል።

በቅርቡ በታላቅ ድምቀት የተጠናቀቀውና በመስቀል አደባባይ የተካሄደው 19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶንን ጨምሮ ከተማዋ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የብስክሌት፣ የአትሌቲክስ፣ የጎዳና ላይ ሩጫን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ መዲናዋ ምቹ ፥ እና ተመሪጭ ከተማ መሆኗን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

አዲስ አበባ አሁን ላይ የስፖርት ልሂቃን መገናኛ ትላልቅ ውድድሮችንና ደጋፊዎችን የምታስተናግድ ደኅንነቷ የተጠበቀና ውብ መዲና ሆናለች ሲል ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑት የተቀናጁ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዕከላት መስፋፋት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።

ይህ የስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ከስፖርታዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ለሆቴል ኢንዱስትሪው፣ ለትራንስፖርት ዘርፉና ለአካባቢው አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ አንቀሳቃሾች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መነቃቃትን መፍጠሩ ተመላክቷል።

ይህም የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የያዘውን ግብ በከፍተኛ ደረጃ እየደገፈው እንደሚገኝም ነው ጽሕፈት ቤቱ ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም