የወልድያ ከተማ የልማት ስኬት ለሌሎች ከተሞች በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ የልማት ትጋትና ቁርጠኝነት ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወልድያ ከተማ የልማት ስኬት ለሌሎች ከተሞች በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ የልማት ትጋትና ቁርጠኝነት ማሳያ ነው
ወልድያ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የወልድያ ከተማ የልማት ስኬት ለሌሎች ከተሞችም በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ የልማት ትጋትና ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረት ልማት ቢሮ ክልላዊ የኮሪደር ልማት የልምድ ልውውጥ እና የግምገማ መድረክ በወልድያ ከተማ እያካሄደ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ ከተሞችን በማልማት፣ በማስዋብና በማሳመር ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው።
በዚህም በኮሪደር ልማትና በሌሎችም ልማቶች ተስፋ ሰጭ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል።
በተለይ የወልድያ ከተማ ችግሮችን ተቋቁማ አስደናቂ ልማት ማከናወን መቻሏ ለሌሎች ከተሞች የልምድና የተሞክሮ ማዕከል መሆን ችላለች ብለዋል።
የከተማዋ የልማት ስኬት ለሌሎች ከተሞችም በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ የልማት ትጋትና ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከከተማዋ አስተዳደር የልማት ቁጭት በመማር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ አተኩሮ መስራት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የዛሬው መድረክም የተሻለ የሰሩ ከተሞች ልምዳቸውን በማካፈል ሌሎች እንዲማሩና እንዲነቃቁ ማስቻል ነው ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው ከህብረተሰቡ ጋር የከተማውን ሰላም በመጠበቅ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በተለይም ከተማዋ በሚፈለገው ልክ አለመልማቷ የፈጠረብን ቁጭት፣ አልህና ጽናት በተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ አስችሎናል ብለዋል።
ወልድያ አሁን እየተሞሸረች፣ የእየደመቀችና ለሁሉም ምቹ እየሆነች ትቀጥላለች ሲሉም አመላክተዋል ።
ለተሞክሮ የሚሆን ተጨባጭ ውጤት ብናስመዘግብም ገና ስለሚቀረን ልማቱን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በመድረኩ በአማራ ክልል የ40 ከተሞች ከንቲባዎች እና የመሰረት ልማት ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።