ቀጥታ፡

ዓለም የዓይኑ ማረፊያ ያደረገው የብራዚል እና የሞሮኮ የዓለም ዋንጫ ተጠባቂ ጨዋታ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6 /2018 (ኢዜአ)፦ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጣምራ አዘጋጅነት የሚካሄደው 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ብራዚል ከሞሮኮ በኒው ጀርዚ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለምን ትኩረት ስቧል።

የዓለም ዋንጫን አምስት ጊዜ ያነሳችው ብራዚል የውድድሩ ቁንጮ እና ስኬታማ ሀገር በመባል ትታወቃለች።

የዘንድሮውን ጨምሮ በሁሉም የዓለም ዋንጫዎች ላይ መሳተፍ የቻለች ብቸኛ ሀገር ናት።

ተጋጣሚዋ ሞሮኮ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ጠንካራዋ ሀገር በመባል እየተሞካሸች ትገኛለች።

የአትላስ አናብስቶች እ.አ.አ በ2022 በኳታር በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዓለም ያስደመመ ብቃት አሳይተዋል።

ሞሮኮ በወቅቱ በታሪክ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያዋ አፍሪካዋ ሀገር መሆን ችላለች። አራተኛ ሆና በማጠናቀቀም አፍሪካ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ምክንያት ሆናለች።

የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።

የዓለም ዋንጫ አድባር የሆነችው ብራዚል እና የአፍሪካ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የያዘችው ሞሮኮ በትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ1998 በፈረንሳይ በተካሄደው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተገናኝተው ብራዚል 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ሮናልዶ፣ ሪቫልዶ እና ቤቤቶ በወቅቱ ለብራዚል ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

እ.አ.አ በ2023 ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ሞሮኮ 2 ለ 1 በማሸነፍ በብራዚል ላይ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች።

እ.አ.አ በ1997 በዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ተገናኝተው ብራዚል 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ብራዚል የዓለም ዋንጫ ስኬታማዋ ሀገር ትሁን እንጂ ውድድሩን ለመጨረሻ ጊዜ ካሸነፈች 24 ዓመታት ተቆጥረዋል።

የደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር እ.አ.አ በ2022 ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ጃፓን በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ጀርመንን 2 ለ 0 በመርታት በማሸነፍ ዋንጫው ካነሳች በኋላ የውድድሩን የክብር ዘውድ መድፋት አልቻለችም።

ሞሮኮ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ያሳየችውን ድንቅ ገድል በዘንድሮውም ለመድገም በምታደርገው ጉዞ ከብራዚል ጋር በመጀመሪያ ጨዋታዋ ተገናኝታለች።

ጨዋታው የጋለ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚሁ በምድብ ሁለት ሃይቲ ከስኮትላንድ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በቦስተን ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በምድብ አራት አውስትራሊያ ከቱርኪዬ ነገ ጠዋት አንድ ሰዓት በቢሲ ፕሌስ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በምድብ ሁለት የ22ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኳታር ከስዊዘርላንድ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ ስታዲየም ምሽት አራት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም