ቀጥታ፡

የሀዋሳ ሀይቅ ዳር ልማት ፕሮጀክት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን አሰናስሎ ሊገነባ ነው

ሀዋሳ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የሀዋሳ የሀይቅ ዳር ልማት ፕሮጀክት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን አሰናስሎ ሊገነባ መሆኑን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚከናወነው የሀይቅ ዳር ልማት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በሀዋሳ ፍቅር ሀይቅ ዳርቻ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የሀዋሳ የሀይቅ ዳር ልማት ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምዕራፍ የፍቅር ሀይቅ፣ አሞራ ገደል፣ አሳ ገበያን የያዘ ሲሆን በዛሬው እለት በይፋ ስራ የሚጀምረው ሀይቅ ዳርቻ ልማት ትልቁ የመዝናኛ ማዕከል መሆኑ ተገልጿል።

በፕሮጀክቱ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሀዋሳ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሃላፊ ኢንጅነር ቸርነት ፍላቴ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ የተለያዩ መገልገያዎችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሬስቶራንቶች፣ ሱቆች፣ የመመልከቻ ማማዎች፣ የዓሳ ማስገሪያ፣ የህዝብ መሰብሰቢያ፣ ሰገነቶች፣ የጎርፍ ውሀ ማጣሪያ፣ የሀይቅ ዳርቻ የብስክሌና የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም ሌሎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀይቅዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱም በስድስት ወራት በጥራት ተገንብቶ ለአገልገሎት የሚበቃ ሲሆን በግንባታው ከ1 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል።

ከጥቁር ውሀ እስከ ታቦር ተራራ 12 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የሀይቅ ዳርቻ ልማት የሚከናወን መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ፣ ሌሎች የክልሉና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሃብቶች፣ ባለሙያዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም