ቀጥታ፡

የተቋማት እመርታ፤ ከመደበኛ አገልግሎት እስከ ከተማ ግብርና ስኬት

ባለፉት ዓመታት እየተተገበረ ያለው የከተማ ግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል።

የከተማ ግብርናን ተግባራዊ ያደረጉ የትምህርት እና የጤና ተቋማትም ዘርፉ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን እያስገኘላቸው መሆኑን ለኢዜአ የገለጹ ሲሆን፤ ዋና ግቡም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማሳከት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ተቋማት ወደ አምራችነት በመሸጋገራቸው፣ መርሃ ግብሩ ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር አበረታች ድሎችን እያስመዘገቡ ይገኛል፡፡


 

በዚህም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የኮልፌ ጤና ጣቢያ ዋና ስራ አስኪያጅ የትምወርቅ ወልደዮሃንስ እንደገለጹት፤ በተቋሙ የከተማ ግብርና የተጀመረው ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ ሰራተኞችን በማሰባሰብ፣ በዶሮ እርባታ እና በጎሮ አትክልት ልማት ላይ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ በላይ ዶሮዎችን በማርባት በቀን ከ800 በላይ እንቁላል እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰው ምርቶቹን ለተቋሙ ሰራተኞችና ለአካባቢው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ጤና ጣቢያው ህክምና ከመስጠት ባለፈ፣ ወደ ተቋሙ የሚመጡ የምግብ እጥረት ያለባቸውን ህጻናት በመለየት ለወላጆችም በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሚገኘው የሚሊኒየም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሉዑልሰገድ ይፋሩ፤ የከተማ ግብርና በትምህርት ቤት ውስጥ መተግበሩ ለተማሪዎች ተግባር-ተኮር የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት ለመስጠት ማስቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በትምህርት ቤቱ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ ሰራተኞች ለገበያ አቅርበው ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መምህር ረታ ብርሃኑም፤ ተግባሩ ተማሪዎች ስለ ግብርና እና ውጤቶቹ ከመሰረቱ እንዲረዱ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መሐመድ ሊጋኒ በበኩላቸው

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሌማት ቱርፋት መርሀ ግብር ተግባራዊ መደረጉ የከተማ ግብርና ስራ በአዲስ አበባ በስፋት የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በከተማው ከ2 ሺህ 700 በላይ በሚሆኑ ተቋማት ላይ የከተማ ግብርና ስራ ቀጣይነት ባለው መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ይህ በየተቋማቱ የተጀመረው አበረታች ተግባር፤ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን እንዲሸምቱ ከማድረጉ ባለፈ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ብሔራዊ ግብ ከዳር ለማድረስ አበርክቶው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም