በወልድያ ከተማ የተመዘገበው የልማት ውጤት ለዕድገት መሰረት የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወልድያ ከተማ የተመዘገበው የልማት ውጤት ለዕድገት መሰረት የሚሆን ነው
ወልድያ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ በወልድያ ከተማ የተመለከትነው የልማት ውጤት በችግር ውስጥም ሆኖ ህዝብን የሚጠቅምና ለእድገት መሰረት የሚሆን ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል ተሞክሮ ያገኘንበት ነው ሲሉ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች ገለጹ።
የአማራ ክልል የ40 ከተሞች አስተዳደር ከንቲባዎችና የከተማና መሰረት ልማት ስራ አስኪያጆች በወልድያ ከተማ የተገነቡ የልማት ስራዎችን ማምሻውን ጎብኝተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት፣ የተከናወነው ልማት ለወልድያ ከተማ አዲስ ፋና የፈነጠቀ ነው።
በጉብኝታችን የኮሪደር፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ሌሎች የልማት ስራዎች በአጭር ጊዜና በጥራት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁ መሆናቸውን ተገንዝበናል ብለዋል።
ይህም የአመራር ቁርጠኝነቱ ካለ በችግር ውስጥም ተሁኖ አስደማሚ የልማት ስራዎችን በማከናወን ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም በበኩላቸው የወልድያ ከተማ በፍጥነት ተለውጣ መመልከቴ ግርምትን ፈጥሮብኛል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የከተማውን ገጽታ በመቀየር አዲስ ውበት ከማጎናጸፋቸው ባለፈ ትልቅ ልምድ የምንቀስምበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የሰራው ልማት የወልዲያ ከተማን ገጽታ በመቀየር አመርቂ ውጤት አስገኝቷል ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ናቸው።
የልማት ስራዎቹ በጥራትና በፍጥነት የተገነቡ በመሆናቸው በችግር ውስጥም ሆኖ ውጤታማ ልማት ማከናወን እንደሚቻል ተምረንበታል ብለዋል።
በጉብኝቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የክልልና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ተሳትፈዋል።