ኮሚሽኑ የጀመረው ጉዞ ስኬታማ ሆኖ የተተለሙ ታላላቅ ሀገራዊ ግቦች እውን እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የጀመረው ጉዞ ስኬታማ ሆኖ የተተለሙ ታላላቅ ሀገራዊ ግቦች እውን እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተጀመረው ጉዞ ስኬታማ ሆኖ የተተለሙ ታላላቅ ሀገራዊ ግቦች እውን እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ውጤታማነት የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኮሚሽኑ አስገነዘበ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ በተለያዩ ምዕራፎች ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል አሳታፊና አካታች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶችን በሰለጠነ ምክክር ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል ምኅዳር መፈጠሩን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ 1 ሺህ 234 ወረዳዎች፣ ክልሎች፣ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ መካሄዱን አንስተዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ የእስካሁን ሂደትም ግልጽ፣ ገለልተኛ፣ አካታችና አሳታፊነቱን ጠብቆ የተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።
ቀጣይም የኢትዮጵያን ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በማካሄድ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ ምክክር ዘላቂ መግባባት ላይ መድረስ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ሳምንታት ያህል በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵውያንም በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተደማምጠው በመመካከር የሚያቀርቧቸው ምክረ ሃሳቦችን በመተግበር ሀገርን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር የሁሉንም የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች ጉባኤው ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደ ሚካሄድበት አዲስ አበባ እንደሚገቡ አስረድተዋል።
የተተለሙ ታላላቅ የኢትዮጵያ የዕድገት ግቦች እንዲሳኩም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የተለመደውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽኑም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተስፋ የጣሉበትን ታሪካዊ የምክክር ሃላፊነት በከፍተኛ ታማኝነት፣ ገለልተኝነትና ቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ ወደ ምክክሩ እንዲቀርቡ ጠይቀው ኮሚሽኑ ተቀብሎ ለማስተናገድ በሩ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።