የኢትዮጵያና ሩሲያ ፍሬያማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አጋርነት የበለጠ እየጎለበተ ነው -አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሩሲያ ፍሬያማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አጋርነት የበለጠ እየጎለበተ ነው -አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ሩሲያ ፍሬያማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር በሁሉም መስክ እየጎለበተ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ገለጹ።
አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሩሲያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
የሀገራቱ ፍሬያማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብርም በሁሉም መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይም የሀገራቱ የሁለትሽ የዲፕሎማሲ ትብብር በትምህርት፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስና በሌሎች ስትራቴጂክ መስኮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮ-ሩሲያ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እየተሻገረ እንደሚገኝ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያና ሩሲያ ዜጎች መካከል እየጎለበተ የመጣው የባህል ልውውጥም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የበለጠ በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
አምባሳደሩ በአዲስ አበባ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት በየዓመቱ የሚከበረው የሩሲያ ቋንቋ ቀንም በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የባህል ዲፕሎማሲ እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል የባህል ልውውጥን ለማሳደግ የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ተግባራትም የዕውቀት ሽግግርን ለማመቻቸት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት በሁሉም መስክ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።