ቀጥታ፡

በዞኑ በመኸር ወቅት ከ264 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይለማል

አፍጥር፣ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ):-በጉራጌ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት ከ264 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ የ2018/19 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት የሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ ''የተቀናጀ ግብርና ለቤተሰብ ብልፅግና'' በሚል መሪ ሃሳብ በቸሃ ወረዳ ተካሂዷል፡፡


 

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው በዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ በመኸር እርሻ ከ264 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል።

ለመኸር እርሻ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው፣ 56 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በመጠባበቂያነት መያዙንም ተናግረዋል፡፡

በመኸር ወቅቱ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ቦለቄ፣ የቢራ ገብስ እና ሌሎች ሰብሎች እንደሚለሙ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም የእርሻ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አበራ ገለጻ በመኸሩ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 41ሺህ 800 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የሚለማ ነው።


 

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሱ ድንቁ በበኩላቸው እንዳሉት በዓመት ከሦስት ጊዜ በላይ ለማምረት የሚያስችል አሰራር በመዘርጋቱ በግብርና ምርት ላይ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው።

የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በወቅቱ ከማሰራጨት ባለፈ የአርሶ አደሩን ፍላጎት እና አቅም በሚገባ በመለየት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተፋሰስ የለሙ አካባቢዎች ጭምር በተለያዩ ሰብሎች እየለሙ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጌታ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙዘፋ የሱፍ ናቸው።

የወረዳው አርሶ አደሮች በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ  በመደረጉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ህይወታቸውን እየቀየሩ መጥተዋል ብለዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዞኑ በሌማት ትሩፋት በተከናወኑ የዶሮ እርባታ፣ የወተት እና የእንስሳት ልማት ስራዎች እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤት  መመዝገቡን ተናግረዋል።


 

በሰብል ልማትም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ያሉት አስተዳዳሪው በተያዘው የመኸር እርሻ አንድም መሬት ጾም እንዳያድር ልማቱን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በበልግ ወቅት በዝናብ ስርጭት መዘግየት ምክንያት የጠፋውን የበቆሎ ሰብልን ለማካካስ አስፈላጊው የግብርና ግብዓት በመጠቀምና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር ይሰራል ሲሉም አክለዋል።

በመድረኩ የተለያዩ ወረዳዎች እና ከተማ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም