የኢትዮጵያ ደህንነትና ብልፅግና ከጎረቤቶቿ የጋራ ተጠቃሚነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ደህንነትና ብልፅግና ከጎረቤቶቿ የጋራ ተጠቃሚነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ደህንነትና ብልፅግና ከጎረቤቶቿ የጋር ተጠቃሚነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያን የድንበር አስተዳደር ሥርዓት ይበልጥ ለማጠናከርና ለማዘመን የሚያስችል ከፍተኛ ሀገራዊ የፖሊሲ ምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት እና ከአፍሪካ ህብረት የድንበር ፕሮግራም ጋር በመተባበር ላለፉት አምስት ወራት ''የኢትዮጵያን የድንበር አስተዳደር ማጠናከር'' በሚል መሪ ሀሳብ ሰፊ የምርምር ፕሮጀክት ሲያካሂድ መቆየቱ ተገልጿል።
ኢኒስቲትዩቱ ጥናቱን መሰረት በማድረግም ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ድንበሮች ከወሰንነት ባሻገር የደኅንነት፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሚንጸባረቅባቸው ስትራቴጂክ ቦታዎች ናቸው።
የኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የድንበር አካባቢ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ቢሆኑም፤ በተለዋዋጭ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ውጤታማ የአስተዳደር መዋቅር የሚጠይቁ ተግዳሮቶችም እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ደህንነትና ብልፅግና ከጎረቤቶቿ የጋር ተጠቃሚነት ጋር የተቆራኘ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የድንበር አስተዳደር ማጠናከር ፖሊሲም ቀጣናዊ የጋራ ትብብርና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሁለገብ ይዘትን አካቶ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።
'የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ በጥናት ላይ የተመሰረተው ፍኖተ ካርታ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ሕይወትና ነባራዊ ሁኔታ ያንጸባረቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችንም በድንበር ተሻጋሪ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አሰራር የሚዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የድንበር አካባቢዎችን ከፀጥታ ስጋት ጋር የሚያያዝ ዕሳቤ በመቀየር የንግድ፣ የፖሊስ፣ ጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽንና የክልል መስተዳድር ተቋማትን ቅንጅት የሚያጠናክር አውድ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የጀርመን ምክትል ቋሚ ታዛቢ ዴቪድ ጉዲሽ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የድንበር ላይ አስተዳደር የፖሊሲ አቅጣጫ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ለዚህም ጀርመን እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮ ከአፍሪካ ህብረትና ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለድንበር አስተዳደር መጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
በቀጣይም የሀገራት ድንበሮች የኢኮኖሚ ትብብር፣ የሰብዓዊ ደኅንነትና የቀጣናዊ ብልፅግና ድልድዮች እንዲሆኑ ድጋፏ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የድንበር አስተዳደር ማጠናከር ፍኖተ ካርታም ድንበር አካባቢዎች የጋራ ሰላምና ደኅንነትን፣ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ድልድይ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።