ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የቡና ምርት ጥራትና ምርታማነት የሚያሻሽሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የቡና ምርት ጥራትና ምርታማነት የሚያሻሽሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለቡና አምራች አርሶ አደሮች የሚውሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የግብርና ግብዓቶች አስረክቧል።


 

ለቡና አምራች አርሶ አደሮች የሚተላለፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የግብርና ግብዓቶችም የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በግብርና መስክ የተመዘገበው ስኬት ለቡና ምርት ጥራትና ምርታማነት ወሳኝ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ የጥራት ቁጥጥር መሳሪያዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ለክልል በማከፋፈል ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ የተደገፉ ግብዓቶች በማቅረብ ጥራቱ የጠበቀ ምርት እንዲያመርቱ በማስቻል የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ግብዓቶቹ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቀረቡ ሲሆን ቡና አብቃይ በሆኑ ክልሎች የተመረጡ ወረዳዎች ለሞዴል አርሶ አደሮች ተደራሽ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

ከዓመታት በፊት በሔክታር 6 ኩንታል ሲመረት የነበረ መሬት አሁን ላይ በሔክታር ከአስር ኩንታል በላይ ቡና ማምረት እየተቻለ መሆኑን አንስተዋል።

በዛሬው እለትም 62 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የግብርና ግብዓቶች ለቡና አምራች አርሶ አደሮች መተላለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ግብዓቶቹ የቡና ምርታማነትንና ጥራትን በማሳደግ አርሶ አደሮችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ጋር እንደሚያላምዱ ጠቅሰዋል።

ቴክኖሎጂዎቹም የቡና ምርታማነት ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ዓለም አፍ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደሚያግዙ አስረድተዋል።

የተሻለ ምርትና ምርታማነት በማረጋገጥ ምርቱ ጥራቱ ጠብቆ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በርክክቡ የተገኙት ኦሮሚያ ክልል ቡናና ሻይ ልማት ዳይሬክተር ታከለ ሃይለማርያም፤የክልሉ መንግስት የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የተሰጡት ግብዓቶችም የበዘርፉ የተሰማሩ እርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው አርሶ አደሩ በአግባቡ የሚጠቀምበት ይሆናል ብለዋል።

የሲዳማ ክልልን ወክለው የመጡት ቡዙነህ ቡናዬ በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ ልዩ ልዩ ዘመናዊ የግብርና ግብአቶች ሲያቀርብ መቆየቱንና በዚህም የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም