ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከቫቲካን ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ እና ከኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ)፡- ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የቫቲካን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ኃላፊ ብፁዕ ወቅዱስ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ጳጳሳቱ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።


 

በቫቲካን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ኃላፊ ብፁዕ ወቅዱስ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ የሥነ-ምግባር እና የሞራል እሴቶች ለሀገሪቷ ትልቅ ሀብት መሆኑናቸውን ተገንዝበዋል።

የሞራል እሴት ኢትዮጵያ በጀግኖች የተሞላች፣ የበለፀገ ሃይማኖታዊ ሥነ-ጽሑፍ፣ ምንኩስና እና ሥርዓተ-ቅዳሴ ያሏት ጥንታዊ ሀገር በመሆኗ ጉብኝታቸውን አስደሳች እንደሚያደርገው ገልጸዋል።


 

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሀገሪቷ ውስጥ በትምህርት እና በጤና መስኮች ላይ በትብብር እንደምትሰራ ጠቅሰው፤ ይህም የሀገሪቷን ተስፋ ሊመጥኑ የሚችሉ የወደፊት ትውልዶችን ለመገንባት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስኬት ያጠናቀቀችውን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክተውም፣ የኢትዮጵያ ጉዞ ሁልጊዜ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ የማይመለስ በመሆኑ እየታየ ያለው የዲሞክራሲ ዕድገት ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና በቫቲካን መካከል ያለው የረዥም ዘመን ታሪካዊ ትስስር በተለያዩ ዘርፎች የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ከቫቲካን ጋር ያላትን ጠንካራ አጋርነት በመጠቀም፣ የልማትና የበጎ አድራጎት ተግባራትን እንደምታከናውን ጠቁመዋል።

በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት ጳጳሳትን ጨምሮ የቫቲካን አምባሳደር ሊቀ ጳጳስ ብራያን አዳይግዌ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም