የዲጅታል ግብርና መስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጅታል ግብርና መስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5 / 2018 (ኢዜአ)፦የዲጅታል ግብርና አሰራር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑ ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዲጅታል ግብርና ከልማዳዊ የእርሻ አሰራር ወደ እውቀትና ቴክኖሎጂ መር ኢንዱስትሪ በመቀየር፣ ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና የግብርና ምርቶችን የውጭ ኤክስፖርት አቅም ማሳደግ የሚያስችል መፍትሄ ነው።
በተጨማሪም ዲጅታል ግብርና ማለት ምርታማነትን ለመጨመርና ፈጣን ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እንደ ኢንተርኔት፣ ድሮን እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በግብርናው ዘርፍ ውስጥ መጠቀም ነው።
የግብርና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዓመታዊ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፎረም አካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ በዚሁ ጊዜ፤ የዘርፉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለሥራ ዕድል፣ ለምግብ ሉዓላዊነትና እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ ሚና ያለው የአገር ውስጥ የጀርባ አጥንት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዘርፉ ለዘመናት በዘመናዊ አሰራር ባለመደገፉ ምክንያት፣ አገሪቱ ካላት እምቅ ሀብት አንጻር የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት መንግስት ዲጅታል የግብርና ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ጠቅሰው ስርዓቱ በተለይ በአርሶ አደሩና በባለሙያው መካከል የነበረውን የመረጃ ልውውጥ ክፍተት በመሙላት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡
አርሶ አደሮች ሬዲዮና የእጅ ስልክን በመጠቀም ስለ አየር ንብረትና ግብዓቶች መረጃ በማግኘት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምርታማነትን ማሳደግ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግና ዘርፉን ለማላቅ የዲጅታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ኤክስቴንሽን መሪ ስራ አስፈጻሚ የኔነሽ ኤጉ በበኩላቸው፤ ድጅታል ግብርና የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ማሳደጉን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው ኋላ ቀር የግብርና አሰራር ስርዓት ወደ ዘመናዊ በማሸጋገር ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡