ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ቡታጅራ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ችግር ፈቺ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ገለጹ፡፡

"የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የሳይንስ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ  በቡታጅራ ከተማ 3ኛው ዙር ክልላዊ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎች አውደ ርዕይ ተከፍቷል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ ትኩረት ተጥቷል፡፡

በክልሉ የሚካሄደው የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ አውደ ርዕይም በዘርፉ ተሰጥኦ ያላቸው የፈጠራ ባለቤቶችን በማበረታታት ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት የመደመር መንግስት እሳቤ ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂና ለፈጠራ ሥራዎች መስፋፋት መሰረት ጥሏል።

በዚህም የዘርፉን  አቅም ወደ ሀብት መቀየር የሚችሉ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ሥራዎች ሁሉንም ዜጋ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መከናወኑንም ጠቁመዋል።


 

ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ትግበራው ስኬታማነት ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ስርዓት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ናቸው።

ለዚህም አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ለሳይንስ፣ ለምርምር፣ ለእውቀት ሽግግር፣ ለቴክኖሎጂና ለኢንዱስትሪ ትስስር፣ ለኢንተፕራይዞች ልማት መስፋፋትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።

የመማር ማስተማር ስራውን ከተለመደው አሰራር በማውጣት በዲጅታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግም የዚሁ አስቻይ ሁኔታ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።

በአውደ ርዕዩ የአፈር ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት መጨመር የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ የምርምር ውጤት ይዘው መቅረባቸውን የተናገሩት  ደግሞ መምህር ታምራት ተስፋዬ ናቸው።

የአውደ ርዕዩ መዘጋጀት የምርምር ስራቸውን እንዲያስተዋውቁና ወደ ገበያ በማውጣት ለውጤታማነታቸው ተጨማሪ አቅም እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።


 

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ክልል አቀፍ የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና የፈጠራ ሥራዎች አውደ ርዕይ የፈጠራ ሥራዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለተሻሉት እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ ታውቋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉና የምስራቅ ጉራጌ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የፈጠራ ባለቤቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም