በዞኑ የባህላዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን የህግ ግንዛቤ በማሳደግ ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የባህላዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን የህግ ግንዛቤ በማሳደግ ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው
ገንዳውሃ፣ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ጎንደር ዞን የባህላዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን የህግ ግንዛቤ በማሳደግ ህብረተሰቡ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ።
በዞኑ በመተማ ወረዳና ገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ስር ለሚገኙ የቀበሌ የባህል ፍርድ ቤት ዳኞችና ፀሐፊዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ዛሬ ተሰጥቷል።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኢብራሂም የሱፍ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት፤ በዞኑ በአገር ሽማግሌ በመዳኘት በሰላም አብሮ የመኖር ባህላዊ እሴትን ከዘመናዊ የህግ እውቀት ጋር ለማጣመር የባህል ፍርድ ቤት ወሳኝ ነው።
በዞኑም ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ከዘመናዊው የፍትህ ዘርፍ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ፍትሀዊነትን ለማስፈን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባህላዊ ዳኞች ጉዳዮችን ከህግ ድንጋጌዎች ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ባህል፣ ወግና አብሮ የመኖር እሴት በጠበቀ መልኩ እንዲከወን ማድረጋቸው በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚፈጠርን የክስ መዝገብ ክምችትና ህብረተሰቡ ፍትህን ለማግኘት ወደ ዞንና ክልል በመመላለስ የሚደርስበትን እንግልትን ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል።
የባህል ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩም ለዳኞችና ሌሎች ባለሙያዎች ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠናና ድጋፍ መስጠቱ እንደሚጠናከርም አረጋግጠዋል።
በዞኑ ሽንፋ ቀበሌ የባህል ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አሰፋ ዋኘው እንደገለጹት በአካባቢያቸው የሚነሱ የመሬት፣ የቤተሰብና የተለያዩ የፍትሐ ብሄር ጉዳዮችን የበደለ ክሶ የተበደለ ተክሶ በዕርቅ እንዲቋጭ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ የተሰጣቸው ስልጠናም ከመደበኛ ህጎች ጋር የሚጣጣሙ አሰራሮችን ለይተው በማወቅ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በገንዳ ውኃ ከተማ ቀበሌ 01 የባህል ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ረዳ ላቀው በበኩላቸው፤ በሚሰጡት የባህል የፍትህ አገልግሎት የህግ እውቀት ሲታከልበት የተበዳዮችን መብት ለማስከበር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የባህል ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚመሰረተው በሁለቱም ባለጉዳዮች ፈቃደኝነት ላይ በመሆኑ በቀልን በማስቀረትና እርቅ በመፈጸም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመመላለስ የሚባክነውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በመቆጠብ ለሌሎች የልማት ስራዎች ለማዋል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።