በሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት በቂ ዝግጅት አድርገናል- ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት በቂ ዝግጅት አድርገናል- ተማሪዎች
ዲላ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ)፡- ዘንድሮ በሚሰጠው 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የዲላ ከተማ ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ።
የከተማው አስተዳደር በበኩሉ በትምህርት ዘመኑ የማለፍ ምጣኔን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት መደረጉን አስታውቋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዲላ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በሀገር አቀፉ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማው የቆፌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቸርነት ዘነበ እንደገለጸው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በተሻለ ውጤት ለማለፍ አመቱን ሙሉ ከጓደኞቹ ጋር በቡድንና በተናጥል ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይ በትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን ማጠናከሪያ ትምህርትና ተከታታይ ምዘና ከራሱ ጥረት ጋር ተዳምሮ ለፈተናው ዝግጁ እንዳደረገው አንስቷል።
በፈተናው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ዓመቱን ሙሉ በተለየ መልኩ ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን የገለጸችው ደግሞ የዲላ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዝናቧ ሚሊዮን ናት።
በግል ጥረት ከማድረግ በተጓዳኝ በቡድን በማጥናትና ፈተናዎችን በመስራት እንዲሁም ማጠናከሪያ ትምህርት በመከታተል እራሷን ዝግጁ ማድረጓን ተናግራለች።
የዲላ ዶንቦስኮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናርዶስ አዳነ ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤት ደረጃ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስዳ ማጠናቀቋ ያለምንም ችግር ፈተናውን በበይነ መረብ ለመውሰድ ዝግጁ እንዳደረጋት ገልጻለች።
በትምህርት ቤቱ የማጠናከሪያ ትምህርት በመውሰድና ተከታታይ ምዘናዎችን በበይነ መረብ በመስራት ለፈተናው ዝግጁ መሆኗንም ገልጻለች።
በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በርትታ ስታጠና መቆየቷን ያነሳቸው ደግሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ፍርቱና የኔነህ ናት።
በአሁኑ ወቅት የትምህርት ክፍለ ጊዜን በማጠናቀቅ ክለሳና የበይነ መረብ ፈተና ልምምድ እያረጉ መሆኑን አንስታ ይህም ለፈተናው በይበልጥ ዝግጁ እንዳደረጋት ተናግራለች።
የዲላ ከተማ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዮሴፍ ሆርዶፋ በበኩላቸው በከተማው ለ2 ሺህ 135 የ12 ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን በበይነ መረብ ለመስጠት የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት ዝርጋታን ጨምሮ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በትምህርት ዘመኑ የማለፍ ምጣኔን ለማሳደግ መምህራን፣ ተማሪዎችና የትምህርት አመራሩ በቅንጅት እየሰሩ መቆየቱን አንስተዋል።
በተለይ የተማሪዎችን አቅም በማጠናከሪያ ትምህርትና ተከታታይ ምዘና ከማዳበር ባለፈ የበይነ መረብ ፈተና አሰጣጥ ጋር እንዲተዋወቁ በአራት ማዕከላት ተከታታይ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም በትምህርት ዘመኑ በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ብለው እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።