ቀጥታ፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለአርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት በማቅረብ ተጠቃሚነቱን የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው

ሰቆጣ፤ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለአርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

በመምሪያው የመሬት አስተዳደር ባለሙያ አቶ ቤተማርያም ሸጋው ለኢዜአ እንደገለፁት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለ330 ሺህ አርሶ አደሮች የ2ኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷል።

ይህም አርሶ አደሩ ደብተሩን በማስያዣነት ተጠቅሞ ገንዘብ በመበደር ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 624 አርሶ አደሮች በይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸው አማካኝነት የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ብድሩ መመቻቸቱም አርሶ አደሩ ከሰብል ልማቱ በተጨማሪ በእንስሳት ማድለብ፣ በወተት፣ በንብ ማነብና በሌሎች የገቢ ማስገኛ የልማት ስራዎች እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ይህም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ተጨማሪ ሃብት ለማፍራት የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

በጋዝጊብላ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ዋጋው ካሴ እንደገለጹት ግማሽ ሄክታር የእርሻ ማሳቸውን በማስያዝ የ99 ሺህ ብር ብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ለልማት እንዲተጉ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመው በተበደሩት ገንዘብም በከብት ማድለብ ስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ሌላዋ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ራሄል ክንፈ በበኩላቸው ብድሩ መመቻቸቱ ከሰብል ልማት ባለፈ በከብት ማድለብና በሌሎች የስራ መስኮች ለመሰማራት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም