በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በአገልግሎት አሰጣጥና በወጣቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ውጤት አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በአገልግሎት አሰጣጥና በወጣቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ውጤት አምጥቷል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በአገልግሎት አሰጣጥና በወጣቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ገለፀ፡፡
የሲዳማ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ በራሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአምስት ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭ በክልሉ በመንግስታዊ አገልግሎትና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ውጤት አምጥቷል።
በክልሉ ሰልጥነው ምስክር ወረቀት ካገኙት ውስጥ የመንግስት ሠራተኞች፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ወጣቶች እንዲሁም ተማሪዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
በክልሉ ብዙ የመንግስት ሠራተኞች የዲጂታል ክህሎት ባለቤት መሆናቸው ውጤታማ መንግስታዊ አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
ሥልጠናውን የወሰዱ ወጣቶችም በአሁን ወቅት በዲጂታል ኢኮኖሚ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን በመጠቀም ገቢ የማግኘት ዕድላቸውን ማስፋታቸውንም አክለዋል።
በክልሉ ሥልጠናውን ወስደው ካጠናቀቁ ዜጎች መካከል በሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ወይዘሮ ሙሉወርቅ መኳንት አንዷ ናቸው።
በተለያዩ ኮርሶች የሚሰጡ የኮደርስ ስልጠናዎችን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት እንደወሰዱ ገልጸው በሥልጠናው የቴክኖሎጂ እውቀታቸው ያሳደጉና ለስራቸው አጋዥ የሆኑ ብዙ ክህሎቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ዲጂታል አሰራር በተለይ ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት ቅልጥፍናና ተደራሽነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረው፣ ስልጠናው በስራቸው አገልግሎቶችን በተሻለ መንገድ ለመስጠት አስችሎኛል ብለዋል።
ወጣት አብርሀም ጥላሁን በበኩሉ በሀዋሳ ከተማ በግል ድርጅት ውስጥ በመተግበሪያ አልሚነት ተቀጥሮ እየሰራ መሆኑን ገልጾ፣ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ሁሉንም ኮርሶች መውሰዱን ተናግሯል፡፡
ድርጅቱ የተለያዩ መተግበሪያዎችን አልምቶ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ እንዲሁም የኔትወርክ ዝርጋታ እና የኦንላይን ገበያ ላይ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል።
በተቋሙ የሚለሙ መተግበሪያዎች ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር አብረው እንዲሄዱ ለማድረግ ብሎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታችን እንዲጨምር የኮደርስ ሥልጠና መውሰዴ ጠቅሞኛል ብሏል፡፡