ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች  ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ፣ እንዲሁም በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት አስታወቀ።

ኢንስቲትዮቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለይ በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል።

በዚህም ምክንያት እርጥበታማ የአየር ሁኔታው በመጠንም ሆነ በስርጭት ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስፋፋ ይሄዳል ብሏል።

በዚህም ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች የሚያመልክቱ ሲሆን በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።

በሚቀጥሉት ቀናት ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎችና የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል።

በተጨማሪም አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና በአካባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።

ከሚኖረው ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ጋር በተያያዘ በተለይም የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በአፋር፣ በደቡብ ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ሥፍራዎች ላይ ከ32 እስከ 41 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቁሟል።

የሚኖረው እርጥበት ለመኸር እርሻ፣ የበልግ ሰብል አብቃይ ለሆኑ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብሏል።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው የገጽ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል።

በዚህም አብዛኛው አባይ፣ ላይኛው እና መካከለኛ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ላይኛው ስምጥ ሸለቆ፣ በጥቂት የገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ከመካከለኛ እስከ ከባድ የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት ይኖራቸዋል ብሏል።

አብዛኛው ተከዜ፣ በጥቂት የላይኛው እና ታችኛው አባይ፣ ላይኛውና መካከለኛው አዋሽ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤሸበሌ እና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸውም ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም