ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል

ነገሌ ቦረና፤ ሰኔ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት አመቱ እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የእቅድና በጀት ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሊበን ሀላኬ፣ በበጀት አመቱ ለ53 ሺህ 26 ወጣቶች የስራ እድል ለማመቻቸት ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በበጀት ዓመቱ እስካሁን 51 ሺህ 669 ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ከተሰማሩበት የስራ መስኮች መካከል በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ንግድና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡት በ2 ሺህ 258 ህብረት ስራ ማህበራት በመደራጀት መሆኑን ጠቁመው፣ ወደ ስራ ከገቡት መካከል 23 ሺህ 189 ሴቶችና የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ወጣቶች ይገኙበታል ብለዋል።

የስራ እድል ተጠቃሚ ለሆኑ ወጣቶች የብድር አገልግሎት መመቻቸቱንም አክለዋል።

ለስራ እድል ተጠቃሚዎቹ በገጠር 458 ሄክታር የማምረቻ ቦታና በከተሞች ደግሞ 38 የመሸጫ ሼዶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።


 

የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ወጣት ኤልያስ ቀንአ፣ በልብስ ስፌት ስራ በመሰማራት የተለያዩ አልባሳትን በማዘጋጀት እንደሚተዳደር ተናግሯል።

በመንግስት የተመቻቸው የማምረቻ፣ የመሸጫ ቦታና የብድር አቅርቦት ለስራችን ስኬት እገዛ እያደረገልን ነው ብሏል ወጣቱ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም