ቀጥታ፡

የጤና ዘርፍ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በላቀ ብቃት መምራት የሚያስችል ውጤታማ የተግባቦት ስራዎች መጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በላቀ ብቃት መምራት የሚያስችል ውጤታማ የተግባቦት ስራዎች መጠናከር እንደሚገባቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ''ውጤታማ ተግባቦት ለጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የስልጠና መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

ለጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና የኮሙኒኬሽን ሙያተኞች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሚሰጠው ስልጠና ከዛሬ ሰኔ 5 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ተገልጿል።

መድረኩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፣ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፤ ስኬታማ ተግባቦት የውጤታማ መሪ መለያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አሁን ላይ የጂኦ ፖለቲካና የጤናው ስነ ምህዳር እየተለወጠ መምጣቱን ያገናዘበ ተግባቦት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም የጤና ዘርፍ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ተግባቦት ለህብረተሰብ ደህንነት ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

የጤና ባለሙያ በእያንዳንዱ ዜጋና ትውልድ ህይወት ላይ የራሱ አስተዋጽኦ ያለውና አሻራ ያሳረፈ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለሙያዎቹ በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና በመረዳት የተግባቦት ስራቸውን በአግባቡ መምራት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የተደረጉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ዓለምአቀፍ ትኩረትን የሳበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጤናው የተጠበቀ፣ ምርታማና ውጤታማ ዜጋ ለመፍጠር የጤናው ዘርፍ ከተግባቦት ጋር የተሰናሰለ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለፉት ዓመታት በትርክት ግንባታና ህብረተሰብን ማስተማር የሚያስችሉ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።

ተቋሙ ከህትመት ባሻገር የኮሙኒኬሽን አቅም የመፍጠርና ትርክት ግንባታ ላይ የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም