ቀጥታ፡

በዓለም ዋንጫው ሊታዩ የሚገባቸው 10 ተጫዋቾች

በሙሴ መለሰ    

በስተመጨረሻም ታላቁ የዓለም ዋንጫ ትናንት ተጀምሯል። በአሜሪካ ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት የተጀመረው የ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ብሔራዊ ቡድኖችን በማሳተፍ 104 ጨዋታዎችን በ16 ስታዲየሞች ያካሂዳል። አዲሱ የውድድር ፎርማት አዳዲስ ኮከቦች ደምቀው እንዲወጡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

መላው ዓለም ትኩረቱን ወደ ሰሜን አሜሪካ በሚያደርግበት በዚህ ወቅት፤ የእግር ኳስ ተንታኞች በልዩ ትኩረት ሊታዩ ይገባቸዋል ብለው የመረጧቸውን 10 ኮከብ ተጫዋቾች የተመለከቱ መረጃዎች ይዘን ቀርበናል።

1.ሊዮኔል ሜሲ (አርጀንቲና)

ብዙዎች የወቅቱ ሻምፒዮን አርጀንቲና ጉዞዋ የሚወሰነው በሜሲ ብቃት ላይ ነው እያሉ ይገኛል። በ38 ዓመቱ ይህ ምናልባትም የመጨረሻው የዓለም ዋንጫው ሳይሆን አይቀርም። ሜሲ ጨዋታውን የሚያደርገውም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ሶከር ሊግ ኢንተር ማያሚን ወክሎ በፕሮፌሽናል ደረጃ በሚጫወትባት ሀገር ላይ ነው።

አርጀንቲና አሁንም ዋንጫውን ለማንሳት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ ሜሲ ለዚህ እንደ ትልቅ ምክንያት ይነሳል።

የመጨረሻውን ስኬታማ ጉዞ የማድረግ ዕድሉ እና ምናልባትም ከረጅም ጊዜ ተቀናቃኙ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር በዓለም ዋንጫ መድረክ የመገናኘት አጋጣሚ፣ ይህንን ውድድር የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።

2.ክርስቲያኖ ሮናልዶ (ፖርቱጋል)
ስለ ሮናልዶ ካነሳን አይቀር ልክ እንደ ሜሲ ሁሉ፣ ይህ በ41 ዓመቱ የሚጫወተው ስድስተኛው (ክብረ ወሰን የሆነ ተሳትፎ) እና ምናልባትም የመጨረሻው የዓለም ዋንጫው ይሆናል። በዚህ ዕድሜው በውድድሩ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ቢያስነሳም፣ ፖርቱጋል እስካሁን የዓለም ዋንጫን አሸንፋ አታውቅም።

ሮናልዶ በታሪክ የምንጊዜም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ለመባል ይህንን ዋንጫ ማሸነፍ ይኖርበታል። ፖርቱጋል በውድድሩ ላይ እጅግ ጠንካራ እና ጥልቅ ስብስብ ያላት ቡድን ስትሆን፣ ዋንጫውን ካነሳች  ሮናልዶ የሁሉ ነገር ማዕከል ይሆናል።

3. ላሚን ያማል (ስፔን)

የዓለም ዋንጫው የትውልድ ቅብብሎሽ ወቅት ሊሆን ይችላል። ሜሲ እና ሮናልዶ ከመድረኩ ሲሰናበቱ፣ ተተኪነቱን ለመረከብ ዝግጁ የሆነው የ18 ዓመቱ ድንቅ ታዳጊ ብቅ ብሏል። ስፔን በውድድሩ ላይ ዋንጫውን ለማንሳት ቀዳሚ ግምት ባገኘችበት በዚህ ወቅት፣ ያማል በባርሴሎና ቤት 16 ጎሎችን አስቆጥሮ 11 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማዘጋጀት የላሊጋው የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን ተቀዳጅቷል።

እንዲሁም የኮከብ ግብ አግቢነት (ጎልደን ቡት) ሽልማትን ለማግኘት ከሚጠበቁት ተጫዋቾች መካከል  አንዱ ነው። ይህ ውድድር ያማል የዓለም እግር ኳስ ቁንጮ መሆኑን የሚያስመሰክርበት ትልቅ ዕድል ነው።

4. ኪሊያን ምባፔ (ፈረንሳይ)
ከስፔን በመቀጠል ፈረንሳይ ውድድሩን የማሸነፍ ሰፊ ዕድል እንዳላት ይታመናል። ከአራት ዓመታት በፊት በአርጀንቲና በመለያ ምት ተሸንፋ ዋንጫውን ለማጣት ተገዳለች። ቢሆንም፣ ምባፔ ያንን ውድድር በስምንት ጎሎች እና በሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሽልማትን ወስዷል።

አሁንም ያንን ክብር የመድገም ግምት ተሰጥቶታል ። በአሁኑ ወቅት የ27 ዓመቱ ወጣት ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ከሪያል ማድሪድ ጋር 56 ጎሎችን አስቆጥሯል። ፈረንሳዮች የዓለም ዋንጫውን የሚያነሱ ከሆነ፣ ከድሉ ጀርባ የሚነሳው ምባፔ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

5. ሃሪ ኬን (እንግሊዝ)
ዋንጫው በመጨረሻ ወደ እንግሊዝ ይመለስ ይሆን?  ሶስቱ አናብስቶች  እ.አ.አ ከ1966 በኋላ የዓለም ዋንጫን ማሸነፍ አልቻሉም፤ እንዲሁም እንደ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ኮል ፓልመር፣ ፊል ፎደን እና ሃሪ ማጉዋየር ያሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን በዚህ ውድድር ላይ ሳይጠሩ ቀርተዋል።

ነገር ግን ኬን አሁንም በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ሲሆን፣ እ.አ.አ በ2025/26 የውድድር ዓመት ለባየር ሙኒክ እና እንግሊዝ ባደረጋቸው 57 ጨዋታዎች ላይ 67 ጎሎችን አስቆጥሯል።

እንግሊዝ የዓለም ዋንጫውን ለማንሳት እና ተፎካካሪ ለመሆን ከፈለገች ፣ የኬን ግቦች እጅጉን ያስፈልጓታል።

6. አርሊንግ ሃላንድ (ኖርዌይ)

ኖርዌይ ማንም ዋንጫውን ታነሳለች ብሎ የማይጠብቃት፣ ነገር ግን ሳይጠበቁ አስገራሚ ነገር ሊሰሩ ይችላሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በምድብ ዘጠኝ ከፈረንሳይ፣ ሴኔጋል እና ኢራቅ ጋር ተደልድላለች።

ኖርዌያውያን ያለ ጫና ሩቅ ርቀት መጓዝ የሚችሉ ሲሆን፣ ለዚህም የአንበሳውን ድርሻ ከሚወስዱ ተጫዋቾች መካከል የማንችስተር ሲቲው የፊት መስመር ተሰላፊ አርሊንግ ሃላንድ ይሆናል።

ሃላንድ ለኮከብ ግብ አግቢነት ከሚጠበቁት ግንባር ቀደም ተጫዋቾች አንዱ የሆነበት የራሱ ምክንያት አለው። ለኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን በ50 ጨዋታዎች 55 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ዕድሜው ገና 25 ዓመት ብቻ ነው።

7. ቪኒሺየስ ጁኒየር (ብራዚል)
ብራዚል ከማንኛውም ሀገር በላይ ብዙ ጊዜ (አምስት) የዓለም ዋንጫዎችን ያነሳች ሲሆን፣ ወደ እያንዳንዱ ውድድር የሚገቡትም ለማሸነፍ በማሰብ ነው።

እንደ ኔይማር፣ ካሴሚሮ፣ ማርኪኒዮስስ እና ፋቢንሆ ያሉት አንጋፋ የብራዚል ከዋክብት የዕድሜ መግፋት፣ ወጣቱ ቪኒሺየስ ጁኒየር ወደ ፊት መጥቶ የሴሌሳኦ ወሳኝ ተጫዋች የመሆን ዕድል ይሰጠዋል።

ቪኒ በዘንድሮው የውድድር ሪያል ማድሪድ 16 ጎሎችን አስቆጥሮ 5 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቷል፤ በ25 ዓመቱ የቀጣዩ ወርቃማ ትውልድ የእግር ኳስ ከዋክብት ተምሳሌት ሆኗል።

ይህ ውድድር ቪኒሺየስ ከታላላቆቹ ተርታ ለመቀመጥ የሚመጥን የዓለም ቁንጮ ተጫዋች መሆኑን የሚያረጋግጥበት ትልቅ ዕድል ነው።

8. ኡስማን ዴምቤሌ (ፈረንሳይ)
ዴምቤሌ እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዓመት ከፒኤስጂ ባደረገው አስደናቂ ጉዞ በ49 ጨዋታዎች 33 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን 15 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። በዚህም  የባሎን ዶር ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። ከበድኑ ጋር ለተከታታይ ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል።

ትኩረቱ ሁሉ በምባፔ ላይ መሆኑ ባይካድም፣ የፈረንሳይ አደገኛነት ይበልጥ የሚያጎላው ሌላኛው አቅም የዴምቤሌ ፈጠራ እና ሁለገብነት ነው።በተሰጥኦ ረገድ በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

9. ያም ዲዮማንዴ (ኮትዲቯር)
የዓለም ዋንጫ አንዱ መገለጫ ሁሌም አዳዲስ ኮከቦችን ይዞ ብቅ ማለቱ ነው። ዲዮማንዴ ደግሞ በዚኛው ዓለም ዋንጫ ትኩረት ከሳቡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ኮትዲቯር ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ መካከል ባትመደብም፣ ጀርመን፣ ኢኳዶር እና ኩራሳዎ በሚገኙበት ምድብ አምስት ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድል አላት።

ዲዮማንዴ ገና የ19 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ባለፈው የውድድር ዓመት በጀርመኑ ቡንደስሊጋ አርቢ ላይፕዚግ በ28 ጨዋታዎች 12 ጎሎችን በማስቆጠር እና 8 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ደምቋል። ደጋፊዎች ስሙን ገና ላያውቁት ይችላሉ፣ ነገር ግን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሁሉም ብቃቱን ሲመለከቱ ስለ እሱ ማውራታቸው የማይቀር ነው።

10. ቪቲንሃ (ፖርቱጋል)

በፓርቹጋል የመሐል ሜዳ ክፍል ውስጥ ኳስን በመረዳት እና በመፍጠር አቅሙ ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ቪቲንሃ ነው። በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የጨዋታ አቀጣጣዮች አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ባለፈው ዓመት በባሎን ዶር ድምፅ አሰጣጥ ከዴምቤሌ እና ያማል በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በቅርቡም ፒኤስጂ አርሰናልን አሸንፎ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ባነሳበት የፍጻሜ ጨዋታ የኮከብ ተጫዋች (Player of the Match) ክብርን አግኝቷል።

ሮናልዶ የጋዜጣዎችን አርዕስተ ዜና ሊቆጣጠር ይችላል፣ ነገር ግን ፖርቱጋል በውድድሩ ላይ ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደምትችል የሚወስነው የቪቲንሃ የጨዋታ ፍሰት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም