ስምምነቱ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልና ዲያግኖስቲክ ግሩፕ የጀመረውን ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለማላቅ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስምምነቱ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልና ዲያግኖስቲክ ግሩፕ የጀመረውን ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለማላቅ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ በመከላከያ ሚኒስቴር እና በፓዲያት የጤና አገልግሎት ግሩፕ የተፈረመው ስምምነት የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልና ዲያግኖስቲክ ግሩፕ የሚሰጠውን ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ አስታወቁ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ፓዲያት የጤና አገልግሎት ግሩፕ ከተሰኘ የሕንድ ዓለምአቀፍ ኩባንያ ጋር የጤና ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ግሩፑ የላቀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዓለምአቀፍ ተሞክሮ ካላቸው የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር የሕክምና ተደራሽነትን ለማሻሻል እንደሚሠራ ተገልጿል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ የጤና ኢንዱስትሪውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ትብብር ወይም ሽርክና ነው።
የትብብር ስምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም መርቀው በይፋ ሥራ ያስጀመሩት የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልና ዲያግኖስቲክ ግሩፕ ለሰራዊቱና ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ገልጸዋል።
የሆስፒታሉን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትና ተደራሽነት ለማሳደግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጤና ግሩፕነት እንዲዋቀር ውሳኔ መተላለፉን ገልጸው፤ የዛሬው ስምምነት ውሳኔውን ገቢራዊ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የተቋሙን የህክምና መሰረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በማሳደግ ዓለም የደረሰበትን የላቀ የጤና አገልግሎት በኢትዮጵያ መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት ለማረጋገጥና የጤና ተደራሽነቱን ለማሳደግ ከግንባር መስመር እስከ ሪፈራል ሆስፒታል የጤና መሰረተ ልማት በመገንባት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ማድረጉን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የሁለቱ ተቋማት ስምምነት መንግስት ለሕዝቡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የገባውን ቃል ተግባራዊ ያደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ ከሀገር ባለፈ የአፍሪካን የጤና ቱሪዝምን ማጠናከር ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ መከላከልን እና አክሞ ማዳንን መሰረት ባደረገ የጤና ፖሊሲዋ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በውጤታማነት እያሰፋች እንደምትገኝም አንስተዋል።
የፓዲያት የጤና አገልግሎት ግሩፕ ሊቀ መንበር ዶክተር ሀዚብ ራህማን፤ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከርና የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ ለማዘመን ሚናቸውን እንደሚወጡም ነው የጠቆሙት።
በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና ሕንድ መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መምከራቸውን አስታውሰው፤ የጤና ዘርፍ ትብብር ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተፈረመው ስምምነት የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው የላቀ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።