የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጎናል-የኢሉአባቦር ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጎናል-የኢሉአባቦር ዞን አርሶ አደሮች
መቱ ፤ ሰኔ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በኢሉአባቦር ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
የኢሉአባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቋል።
የዞኑ አርሶ አደሮች እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ ልማቶች የአካባቢያቸውን ልምላሜ ከማሳደግ ባሻገር የኢኮኖሚ ምንጭም እየሆናቸው ነው።
በዞኑ የሁሩሙ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በላቸው ዓለማየሁ፣ በአረንጓዴ አሻራ ጥምር ጠቀሜታ ላላቸው ችግኞች የተሰጠው ትኩረት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገው ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በግል ይዞታቸው ላይ የተከሏቸው የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች አሁን ላይ በሚገባ አፍርተው ለምግብነት ከማዋል ባለፈ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው አስረድተዋል።
አቶ ተካልኝ ታደገ የተባሉት ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው፤ በልቅ ግጦሽና በጎርፍ ምክንያት ተጎድቶ የነበረው ይዞታቸው በአረንጓዴ አሻራ አገግሞና ለምነቱ ተመልሶ ለግብርና ልማት በማዋል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግል ይዞታቸው ላይ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በማልማት ከምርት ሽያጭ በዓመት እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ኑሯቸውን ማሻሻል እንደቻሉ አመልክተዋል።
አቶ አይናለም ኪዳኑና አቶ ኢሳያስ አሰፋ የተባሉ የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙና ልምላሜ እንዲላበሱ ከማድረግ በዘለለ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆናቸው ይገኛል።
ተግባሩን ለማጠናከርም አሁን ላይ የችግኝ ጉድጓዶችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸውን ዕፅዋት ለመትከል ማቀዳቸውን አክለዋል።
የኢሉአባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች ለግብርና ሥራ ምቹ የአየር ሁኔታ ፈጥሯል።
ለዜጎችም የምግብ ዋስትናና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ይህንን ለማስቀጠል እንዲቻልም ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ መትከያ ጉድጓድና የችግኝ ማጓጓዝ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በዞኑ ከ254 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ያነሱት ኃላፊው በዚህም 54 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።