ቀጥታ፡

የዞኑ አርሶ አደሮች የተሟላ የግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ ነው

ጭሮ፤ ሰኔ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ በዘንድሮው መኸር አዝመራ የተሟላ የግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ  መሆኑን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የገመቺስ እና ጭሮ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በዞኑ እስካሁን 300 ሺህ ሄክታር መሬት ቶሎ በሚደርሱ ሰብሎች መሸፈኑን አስታውቋል።

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ሰብል እንክብካቤ ድረስ የተሻለ ምርት ለማግኘት በቡድን እየሰሩ ነው።

የገመቺስ ወረዳ የቁኒ ሶጋሪያ ቀበሌ አርሶ አደር ፀጋዬ ታረቀኝ እንዳሉት፤ በዘንድሮ መኸር በአንድ ሄክታር ይዞታቸው ላይ በቆሎ፣ ማሽላና አትክልት እያለሙ ነው።

ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በአግባቡ በመጠቀም በመስመር መዝራታቸውን ጠቅሰው፣ ቡቃያውንም ከአረም ለመከላከል በቡድን እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለቤት ውስጥ የኃይል አቅርቦት ባዮጋዝ እንደሚጠቀሙ የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ተረፈ ምርቱን ደግሞ ለሰብል፣ ለጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በማዳበሪያነት በመጠቀም ወጪያቸውን ለመቀነስ መቻላቸውን አስረድተዋል።

ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር ጥበቡ ወንድሙ በበኩላቸው፤ ግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ግብዓት በመጠቀም በቆሎ በመዝራት ሰብሉን እየተንከባከቡ ይገኛሉ።

ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመከተል እና በቂ ግብዓት በመጠቀም ከዘሩት ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

በጭሮ ወረዳ አርበረከቴ ቀበሌ አርሶ አደር አብዲ አሽም፤ በመኸሩ የእርሻ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ጤፍ፣ ማሽላ እና በቆሎ እየዘሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እስካሁንም አብዛኛው ማሳቸውን የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም በመስመር መዝራታቸውን ጠቁመዋል።

የገመቺስ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ጁሀር ኢብራሂም፤ የወረዳው አርሶ አደሮች ሙሉ የኤክስቴንሽን ፓኬጅ ተጠቅመው ምርታማ እንዲሆኑ በቅርበት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ከበደ ገምታ በበኩላቸው፤ በ2018/2019 የመኸር እርሻ ከ490 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል ብለዋል።

በ15 ወረዳዎች እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከዕቅድ በላይ ከ550 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደጋግሞ በማረስ ለዘር ማዘጋጀት መቻሉን አውስተዋል።

ከዚህ ውስጥም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ማሳ ቀድመው በሚዘሩ እንደ ለውዝ፣ ማሽላ እና በቆሎ ዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።

ለልማቱ ማስፈጸሚያ ከ131 ሺህ ኩንታል በላይ ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በጽሕፈት ቤቱ የግብርና ሜካናይዜሽን እና ግብዓት አጠቃቀም የሥራ ሂደት መሪ አቶ አሰበ ደሬሳ ናቸው።

እስካሁንም 80 ሺህ ኩንታል የሚሆን ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዞኑ በመኸር አዝመራው 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም