ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንትና የንግድ ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንትና የንግድ ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢኮኖሚ እና በፋይናንስ ዘርፍ፣ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር፣ በኢንቨስትመንት፣ ተቋማዊ ፤የሕግጋትና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት፣ በሬሜታንስና በማህበራዊ ድጋፎች ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ተግባራዊ መደረጉ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ላይ በበለጠ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፥ በፍራንኮ ቫሉታ መመሪያ ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ለሀገር የሚጠቅሙ ምርቶችን እንዲያስገባ መፈቀዱ የዳያስፖራውን የንግድ ተሳትፎ ያሳድጋል ነው ያሉት።

የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ የተደረገው ማሻሻያ በሕጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ (ሬሜታንስ) በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማድረጉንም ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ባንኮች ከ20 ሺህ በላይ አዲስ አካውንት መክፈታቸውን ነው አምባሳደር ፍጹም የጠቆሙት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሌሎች ግዙፍ መሰረተ ልማቶች አገልግሎት መጀመራቸው ምቹ ምህዳር በመፍጠር የዳያስፖራውን ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንደሚያሳድጉም ጠቅሰዋል።

የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎች መስፋፋት ዳያስፖራው ሀገሩን መጥቶ እንዲጎበኝና አማራጭ የኢንቨስትመንት መስኮችን እንዲያጤን በር ከፋች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራዎች ለጉብኝትና ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ይህም በሀገር ልማትና ኢንቨስትመንት ላይ ያላቸውን ተነሳሽነት ያሳድጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም