ቀጥታ፡

መንግስት ጠንካራ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሥርዓት ገንብቷል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት አቅም የሚፈጥሩ ሙያተኞችና ቴክኖሎጂዎች ውጤታማ የሚሆኑበት ጠንካራ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሥርዓትና ምቹ ምኅዳር መገንባቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ የመጀመሪያውን ዓለምአቀፍ የምርምር ጉባኤ እና የቴክኖሎጂ ውድድር ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር)፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ሀገራት የመጡ ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

በመክፈቻው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)፤ መንግስት ጠንካራ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሥርዓትን በመገንባት፣ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት አቅም የሚፈጥሩ ሙያተኞችና ቴክኖሎጂዎች ውጤታማ የሚሆኑበት ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል ብለዋል።

ከሀገራዊ የልማት እድገት ጋር የተናበበ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲጎለብት መንግስት የዘርፉን እድገት የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችና አሰራሮች ተግባራዊ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዘርፉ ብቁ ሙያተኛን በማፍራትና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለኢንዱስትሪላይዜሽን እድገት ምላሽ የሚሰጥ፣ አካታችና ጥራት ያለው የቴክኒክና ሙያ ሥርዓት መገንባት የሚያስችል ምኅዳር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ብቁ፣ ቴክኖሎጂ የሚያፈልቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ሰልጣኞችን በማፍራት በኩል አበረታች ለውጥ መመዝገቡን አክለዋል።

ለእነዚህ ስኬቶች ዋና ምክንያት ከሆኑት መካከል ገበያ መር ሥልጠና፣ የኢንዱስትሪ ተሳትፎ፣ አካታችነት፣ ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም የፈጠራ እና የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ማጎልበት በመቻሉ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የኢንዱስትሪላይዜሽን እድገትን ለማፋጠንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ጠንካራ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓትን ማጠናከርና ከዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር በጋራ መስራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የቴክኖሎጂ ምርምር ሥራዎች ወሳኝ በመሆናቸው፣ ዛሬ የተጀመረው ዓለም አቀፍ ጉባኤና የቴክኖሎጂ ውድድር የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲጎለብት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።


 

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በተዘጋጀው የሦስት ቀናት ጉባኤ ዘርፉ ላይ ያተኮሩ የምርምር ጽሑፎች እንደሚቀርቡና የተመረጡ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ለውድድር እንደሚበቁ አብራርተዋል።

በዚህ ታላቅ ሁነት ላይ ከ16 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም