ቀጥታ፡

በክልሉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ምቹ ለማድረግ የዲጂታል አገልግሎት ዝርጋታ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዳማ፤ ሰኔ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ምቹና ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል አገልግሎት ዝርጋታ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ገለጸ።

በኤጀንሲው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙስባሁዲን አብዱልመጅድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ምቹና ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል አገልግሎት ዝርጋታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።

በዚህም መሠረት በበጀት ዓመቱ የታሪፍ ተመን፣ የሚሸፈኑ መስመሮች ርቀት እንዲሁም የትራንስፖርት መነሻና መዳረሻዎች በግልጽ እንዲታወቁ ተደርጓል ብለዋል።

አሽከርካሪዎችና ረዳቶችም ይህንን አሠራር እንዲከተሉ ከማድረግ ባለፈ ተሽከርካሪዎች በተፈቀደላቸው የሥምሪት መስመር ብቻ እንዲሠሩ፣ ቦሎና የሦስተኛ ወገን መድን መለጠፋቸውን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም የቴክኒክ ብቃትና የሥምሪት ፈቃድ ቁጥጥር ሥርዓቶች መጠናከራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ተመሳሳይ ርቀት ያላቸው ጉዞዎች ተመሳሳይ የታሪፍ ክፍያ እንዲኖራቸውና ተሽከርካሪዎች ወርሃዊ ሥምሪታቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ የዲጂታል ሥምሪት አሠራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

በተለይም የሕዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም እንዲሁም አገልግሎቱን ለማዘመን የተቀናጀ የዘመናዊ መናኸሪያዎች ልማት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በጅማ፣ ነቀምቴ፣ ወሊሶ፣ ሮቤና ሻሸመኔን ጨምሮ በ17 የክልሉ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መናኸሪያዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስረድተዋል።

መናኸሪያዎቹ ከብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በሲሲቲቪ (CCTV) ካሜራ የተደገፈ ቀጥታ ቁጥጥርና ክትትል ከኤጀንሲው ዋና ማዕከል እየተደረገባቸው ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም በቡሌ ሆራና በአሰላ ከተሞችን ጨምሮ የአራት አዳዲስ ዘመናዊ መናኸሪያዎች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖችና 23 ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ከ380 በላይ የሕዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያዎች ላይ ዲጂታል የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።

ቅጣት ያለባቸው አሽከርካሪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ክፍያ መፈጸም የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም አክለዋል።

ኤጀንሲው በቀጣዩ በጀት ዓመት አገልግሎቱን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙስባሁዲን፤ ተገልጋዮች በቴሌብር አማካኝነት ካሉበት ሆነው የሚፈልጉትን ተሽከርካሪ የጉዞ ትኬት መቁረጥ የሚችሉበትን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም