የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያ አስተማማኝ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ለሆነው ሀገራዊ ምክክር ስኬት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመ ነፃ ተቋም ሲሆን፣ በሀገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።
እስካሁን ባለው ሂደት ከወረዳ ጀምሮ መላውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን፣ ምሁራንንና ሁሉም ባለድረሻ አካላትን ያሳተፈ ሰፊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር አከናውኗል።
ተቋሙ እነዚህን የተደራጁ አጀንዳዎች ይዞ ወደ ቀጣዩ ወሳኝ ምዕራፍ ለመሻገር፣ በቅርቡ ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻ የዝግጅት ሥራዎቹን እያጠናቀቀ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡
ሀገሪቱ ለዘመናት ከቆዩ ማነቆዎች ተላቃ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ትልቁና አስተማማኙ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ በምክክር ሂደቱ ላይ በንቃት ከመሳተፍ ባለፈ፣ በሁለት ዙር ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰበሰቡትን ሀገራዊ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከቡን አስታውቀዋል።
በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ዋናው ሀገራዊ የውይይት ጉባኤ ላይ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የቆዩና ለአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ሥር የሰደዱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኝ ሙሉ እምነት እንዳላቸውም አብራርተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2018 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫና በሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ላይ በልዩ ዕቅድ መነሳቱን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ኮሚሽኑ በከፍተኛ ኃላፊነት እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር ያላቸውን የቅርብ የሥራ ግንኙነትና ሀገራዊ ኃላፊነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመጠቆም፣ አሁን ባለው ወሳኝ ወቅት ለጋራ መግባባት መሠረት መጣል የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ይህንን ታሪካዊና ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበትን ሀገራዊ ሂደት በንቃት በመደገፍ፣ ሀገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ማነቆ ወጥታ ወደ አዲስ የመረጋጋትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምዕራፍ እንድትሻገር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡