የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች፦ ካናዳ ከቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና፣ አሜሪካ ከፓራጓይ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች፦ ካናዳ ከቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና፣ አሜሪካ ከፓራጓይ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሁለተኛ ቀን መርሃ ግብሩ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በምድብ ሁለት ካናዳ ከቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና ምሽት አራት ሰዓት ላይ በቶሮንቶ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከጣምራ አዘጋጆቹ አንዷ የሆነችው ካናዳ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሰሜን አሜሪካዋ ሀገር እ.አ.አ በሜክሲኮ በተካሄደው 13ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እና ከአራት ዓመታት በፊት በኳታር በተደረገው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ አድርጋለች።
ካናዳ በውድድሩ ላይ እስከ አሁን ባደረጋቻቸው ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዳለች።
ቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና እ.አ.አ በ1992 ነጻነቷን ካወጀች በኋላ በዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የደቡብ ምስራቅ አውሮፓዋ ሀገር በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ጣልያንን በመለያ ምት በማሸነፍ ለውድድሩ ማለፏ ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ2014 በብራዚል በተካሄደው 20ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ነው።
ቦሲኒያ በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጋ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዳለች።
ብቸኛ ድሏ የተመዘገበው ኢራንን 3 ለ 1 በማሸነፍ ነው።
የዛሬው ጨዋታ ካናዳ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሏን ለማስመዝገብ ፤ ተጋጣሚዋ ቦሲኒያ ሁለተኛ ድሏን ለማሳካት የሚያደርጉት ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው የሚኖራቸው ጉዞ የሰመረ እንዲሆን ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
በምድብ አራት አሜሪካ ከፓራጓይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሎስ አንጀለስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ከዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካ በውድድሩ ላይ ስትሳተፍ የአሁኑ ለ12ኛ ጊዜ ነው።
አሜሪካ እ.አ.አ በ1930 በኡራጓይ በተካሄደው የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት አጋጣሚ ትልቁ ውጤቷ ነው።
በውድድሩ ላይ ዘጠነኛ ተሳትፎዋን የምታደርገው ፓራጓይ እ.አ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 19ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችበት ውጤት የተሻለ ርቀት የሄደችበት ተሳትፎዋ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ኡራጓይ እ.አ.አ በ1930 ባዘጋጀችው የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ላይ ተገናኝተው አሜሪካ 3 ለ 0 አሸንፏል።
አሜሪካ እና ፓራጓይ ከ96 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በዓለም ዋንጫው ይገናኛሉ።