ቀጥታ፡

ሶስት ቀይ ካርዶች በታዩበት የዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ጨዋታ  ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን አሸነፈች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን 2 ለ 0 ረታለች።

ትናንት ማምሻውን በአዜቴካ ስታዲየም በተካሄደው የምድብ አንድ ጨዋታ ጁሊያን ኪንዮኔስ በዘጠነኛው ደቂቃ ሜክሲኮን መሪ ያደረገችውን ጎል አስቆጥሯል።

የ29 ዓመቱ አጥቂ ኪንዮኔስ የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ራውል ሂሜኔዝ በ67ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

የደቡብ አፍሪካው ስፔፌሎ ሲቶሌ በ49ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

የውድድሩ የመጀመሪያ ቀይ ካርድ ሆኖ ተመዝግቧል።

በ84ኛው ደቂቃ ሌላኛው የደቡብ አፍሪካው ቴምባ ዝዋኔ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በዚህም ደቡብ አፍሪካ ጨዋታውን በዘጠኝ ተጫዋች ለመጨረስ ተገዳለች።

የሜክሲኮው ሴዛር ሞንቴስ በ92ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

በመክፈቻው ጨዋታ ሶሶት ቀይ ካርዶች መመዘዛቸው አስገራሚ ሆኗል።

በጨዋታው ሜክሲኮ ብልጫ የወሰደች ሲሆን ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር የምትችልባቸውን እድሎች አልተጠቀመችበትም።

በጥልቀት የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ስልት ይዛ የገባችው ደቡብ አፍሪካ የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻለችም።

ከዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሜክሲኮ ውድድሩን በድል ጀምራለች።

ደቡብ አፍሪካ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ሽንፈት አስተናግዳለች።

ከሜክሲኮ እና ደቡብ አፍሪካ ጨዋታ በፊት በአዜቴክ ስታዲየም ደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ተካሄዷል።

በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት መካሄድ የጀመረው 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም