ቀጥታ፡

ቦርዱ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ የሚያደርግበትን የድህረ-ምርጫ ተግባራት ለጋዜጠኞች አስጎበኘ  

አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ የሚያደርግበትን የድህረ-ምርጫ ተግባራት ለጋዜጠኞች አስጎበኘ።

የምርጫ ቦርድ ውጤት ማረጋገጫ ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ሽመልስ ሲሳይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሁሉም ምርጫ ክልሎች የማዳመር ሥራ የተጠናቀቀላቸው ሙሉ ሰነዶች በቀጥታ ወደ ዋናው የቦርዱ ውጤት መረከቢያ ክፍል ይገባሉ።

በመቀጠልም በማረጋገጫ ክፍሉ ውስጥ እያንዳንዱ ዕጩ ያገኘው ድምፅ ዋጋ ካላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ እንዲሁም በዕለቱ በአካል ተገኝተው ከፈረሙ መራጮች ቁጥር ጋር የመጣጣሙ ጉዳይ በጥብቅ  እንደሚፈተሽ ተናግረዋል።


 

አስተባባሪው ዶክተር ሽመልስ እንደገለጹት፤ ይህን የማጣራት ሂደት የሚያልፉ መረጃዎች ተገቢነትና ትክክለኛነታቸውን ወደ ሚያረጋግጠው የኦዲት ቡድን የሚመሩ ይሆናል።

ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠው ደግሞ በቦርዱ የአይሲቲ (ICT) ሲስተም ውስጥ ገብተው በቦርዱ እንዲጸድቁ ይደረጋልም ነው  ያሉት። 

በማረጋገጥ ሂደቱ ላይ ያልተጣጣሙና ግድፈት ያለባቸው መረጃዎች ሲገኙ የኦዲት ቡድኑ በሚገባ ከመረመረ በኋላ ለውሳኔ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ቦርዱም እነዚህን ጥብቅ የአሠራር ሂደቶች በሙሉ ተከትሎ የመጨረሻውን ውጤት ይፋ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም