ቀጥታ፡

ዋና ጠቅላይ መምሪያው ከተሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ የሀገርን ክብር በአደባባይ ከፍ የሚያደርጉ ስፖርተኞችን እያፈራ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከተጣለበት ሰላምን የማስጠበቅ ተልዕኮ በተጨማሪ የሀገርን ክብር በዓለም መድረክ ከፍ የሚያደርጉ ስፖርተኞችን እያፈራ እንደሚገኝ የመምሪያው አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በ2018 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የፖሊስ አባል ስፖርተኞች የማዕረግ እድገት፣ የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም የእውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብር አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤  የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ፍጹም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ለዚህም ለመዲናዋ የፖሊስ አባላት በሙሉ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከተጣለበት ሰላምን የማስጠበቅ ተልዕኮ በተጨማሪ የሀገርን ክብር በዓለም አቀፍ የስፖርት አደባባይ ከፍ የሚያደርጉ ስፖርተኞችን እያፈራ መሆኑንም አስታውቀዋል። 

ከተቋሙ የሚወጡ ስፖርተኞች በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ድልን በመቀዳጀት በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የሀገሪቷ ክብር በዓለም አደባባይ ጎልቶ እንዲታይ አድርገዋል ብለዋል። 

ይህ አበረታች ውጤት ሊገኝ የቻለው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ እንደሆነም ተናግረዋል። 

የተካሄደው የእውቅና መርሃ ግብር ባለድል ስፖርተኞችን ለማበረታታት ያለመ ሲሆን፤ በቀጣይም የፖሊስ ተቋማት የተተኪ ስፖርተኞች ምንጭ ሆነው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም