ቀጥታ፡

ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በግብርና ልማት ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተግባራት አፈጻጸምን የሚገመግም መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል። 


 

በኢንስቲትዩቱ የደቡብ ማዕከል የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ህርባዬ እንዳሉት፤ አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም ግብርና ቢዝነስ ኩባንያዎች በማደራጀት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ለዚህም ማዕከሉ በተመረጡ ወረዳዎች በኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ምርታማነታቸው እንዲያድግና  የገበያ ትስስር እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ኩታ ገጠም እርሻ አርሶ አደሩ የግብአት አቅርቦትን በቀላሉ የሚያገኝበት አውድ ከመፍጠሩ ባለፈ የሜካናይዝድ እርሻን በመተግበር ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ  ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው። 


 

ለዚህም ቢሮው ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች እያደረሰ ይገኛል ብለዋል።

ይህም አርሶ አደሩ የግብርና ምርቶቹን በጥራትና በብዛት ለገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የቸሃ ወረዳ ግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አባል አርሶ አደር አብዱራሃማን ሙክታር፤ ከዚህ ቀደም በተናጠል ባከናወኑት የእርሻ ስራ ብዙም ሳይጠቀሙ ቆይተዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በኩታ ገጠም እርሻ ተደራጅተው ኩባንያ ከፈጠሩ ወዲህ ጉልበታቸውን በማስተባበር እንዲሁም ግብአትና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዳሳደጉ ተናግረዋል።

ይህም ምርታቸውን ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ በማግኘት የቤተሰባቸውን ኑሮ ለማሻሻል እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በስልጤ ዞን የሳንኩራ ወረዳ ግብርና ቢዝነስ ኩባንያ አባል ወይዘሮ አሚና ሃጂ ጀማል በበኩላቸው፤ 85 ወንዶች እና 15 ሴቶች በግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ተደራጅተው የጓሮ አትክልትና ሌሎች ምርቶች እያመረቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

በዚህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እየሆኑ ከመምጣታቸው ባለፈ ገበያን በማረጋጋት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከማዕከላዊ እና ከሲዳማ  ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም