ቀጥታ፡

በክልሉ ተማሪዎች በክልል አቀፍ ፈተናው ውጤታማ እንዲሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተሰርቷል

ወራቤ ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በክልል የተማሪዎችን ብቃትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ በክልል አቀፍ ፈተናው ውጤታማ እንዲሆኑ መሰራቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ክልላዊ የፈተና ዝግጅትን በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ  መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም  በክልሉ አዲሱን  የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ  የተማሪዎችን ብቃትና ተወዳዳሪነት  ማሳደግ  ተችሏል።

የተማሪዎችን ብቃትና ተወዳዳሪነት ለመለካት  ዘንድሮ በሚሰጠው የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናም ከ183 ሺህ 790 በላይ ተማሪዎች እንደሚፈተኑ ተናግረዋል።

በክልል ደረጃ የሚሰጠውን ፈተና ውጤታማ ለማድረግ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲሰራ መቆየቱንም ነው አቶ አንተነህ የገለጹት።

ለዚህም ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ በማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

ተማሪዎች ኩረጃን በመጸየፍ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ በስነልቦና የተሰራው ስራም ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፈተና አስተዳደር ስርዓቱን በተገቢው ለመምራትም 139 በላይ ፈታኝ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የመፈተኛ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ነውያስታወቁት።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም 3ኛው ዙር ክልል አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ ሥራዎች አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ነገ በቡታጅራ ከተማ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

በኤግዚቢሽኑ በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በግል ፈጠራ ባለቤቶች እና በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች ለውድድር እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

የማህበረሰቡን ችግር ለሚፈቱ የፈጠራ ሥራዎች የገበያ ትስስር ከማመቻቸት ባለፈ ማበረታቻና እውቅና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

በክልሉ የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሰኔ 8 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም