ቀጥታ፡

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት ያስችላል

ነቀምቴ፤ ሰኔ 4/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት አሰራርን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል በኦሮሚያ ክልል የነቀምቴ ከተማዋ ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ ገለጹ።

የነቀምቴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

በመርሃ ግብሩ የከተማዋ ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የመንግስት ተቋማት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።

የአገልግሎቱ ዲጂታላይዝድ መሆን ብልሹ አሰራሮችን በማስቀረት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመፍታት ባለፈ የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት እንደሚቆጥብም ተናግረዋል።

የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ማስተናገድ የሚችለው ማዕከል ወደ ሥራ መግባት ማህበረሰቡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ሲያነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ይፈታል ብለዋል።


 

ማዕከሉ የተቋማትን አሰራር በማዘመን በ12 መስኮት 128 አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ መስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸው፣ ከ200 ሺህ በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች እንደሚያገለግል ጠቁመዋል።

በከተማዋ የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቋማትን አሰራር በማዘመን ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት የራሱ ድርሻ እንዳለው በማዕከሉ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ተናግረዋል።


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ ባለሙያዎች መካከል ተሰማ ሙለታ እንዳሉት መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ህብረተሰቡ ሲያነሳው የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት የዘረጋቸው አሰራሮች የሚበረታቱ ናቸው።

ዘመናዊ አሰራሩ ከዚህ በፊት በፋይል መጥፋትና በአሰራር ችግር ይከሰት የነበረን የደንበኛ ምልልስ በመቅረፍ የተገልጋይ እርካታን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

ማዕከሉ ለሥራ ያለውን አመቺነት በመጠቀም የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ በትጋት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።


 

ሌላኛዋ የማዕከሉ ባለሙያ ወይዘሮ ለሊሴ ለታ ማዕከሉ ወደ ሥራ መግባቱ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚስተዋለውን የተገልጋይ እንግልት ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በማቀናጀት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም