ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር አቻ ተለያየ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ዛሬ ባደረገው ጨዋታ ሶስት አቻ ተለያይቷል።

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊዲያ ኢያሱ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ምኅረት አየለ ቀሪዋን ጎል ለኢትዮጵያ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ናማኩላ ጆን፣ ባቢሬ ማርታ እና ያጋላ ፍላቪያ ለዩጋንዳ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ጨዋታው አዝናኝ እና ተመጣጣኝ ፉክክር ተደርጎበታል።

የወዳጅነት መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከዛምቢያ ጋር የምታደርገው ወሳኝ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት አካል መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ከዛምቢያ ጋር ለሚደረገው ዝግጅት ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከትናንት በስቲያ በካፍ የልህቀት ማዕከል ዝግጅት ማድረግ ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዛምቢያ ጋር የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ሰኔ 27 እና ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ያከናውናል።

ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ታልፋለች።

10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም