ቀጥታ፡

በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምርጫው አፈጻጸምና የድህረ ምርጫ ሥራዎችን ከነገ ጀምሮ በቀበሌ ደረጃ ይገመግማል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አፈጻጸምና የድህረ ምርጫ ሥራዎች ግምገማ ከነገ ጀምሮ በቀበሌ ደረጃ ማካሄድ ይጀምራል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የፓርቲው አፈጻጸምና የድህረ ምርጫ ስራዎችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ጌቱ በመግለጫቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ከሌሊት እስከ ሌሊት በመሰለፍ ድምፁን በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው።

በዚህም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በማካሄድ ኢትዮጵያውያን በፅናት አዲስ ታሪክ ጽፈዋል ብለዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ግቦችን አስቀምጦ የምርጫ ቦርድን ህጎች፣ አዋጅና መመሪያዎች ተከትሎ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እና በፉክክር በመንቀሳቀስ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሚያስችሉ ስራዎች በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል።

ከቅድመ ምርጫ እስከ ምርጫው ዕለት የታየውን የአመራሮችና የአባላቱን የላቀ መናበብ፣ መቀናጀትና ቁርጠኝነት ግለቱን ጠብቆ ማስቀጠል አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የድህረ ምርጫ ሥራዎችን በስኬት በመፈፀምም የተጀመረውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የብልጽግና ጉዞ ይበልጥ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን ጨምሮ በሁሉም ወረዳ የሚገኙ የብልፅግና ህብረት አመራሮች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተያዙ መንትያ ግቦችን ለማሳካት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ተግባራት ላይ ተግባቦት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ከነገ ጀምሮም በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች በጠቅላላ ምርጫው አፈጻፀምና የድህረ ምርጫ ስራዎች እንደሚገመገም ጠቁመው፤ በዚህም በክልሉ በገጠር እና በከተማ የሚገኙ የፓርቲው አባላት እንደሚሳተፉ ነው የገለፁት።

በመድረኩ ላይ ፓርቲው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እቅዱ መሠረት በቅድመ ምርጫና በምርጫው ወቅት የነበረውን አፈጻጸም እንደሚገመገም አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በድህረ ምርጫ ወቅትም ትኩረት በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በሚካሄደው ግምገማ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አባላት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ኃላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም