ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ኦብነግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል

ጅግጅጋ፤ ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በሶማሌ ክልል በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ምክትል ሊቀመንበር አሕመድ ያሲን፤ ከለውጡ በፊት በሶማሌ ክልል በነበረው አግላይና ፍትሃዊነት በጎደለው የፖለቲካ ስርዓት ኦብነግ የጫካ ትግል ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር የትጥቅ ትግሉን በመተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ የትግል ሂደት የሃሳብና የፖሊሲ ልዩነቶች እንደተጠበቁ መሆናቸውን አንስተው፤ በሀገር ሉአላዊነት፣ በብሄራዊ ጥቅምና በዜጎች ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ የተለየ አቋምና አመለካከት የለንም ሲሉ አስረድተዋል።

በሶማሌ ክልል በለውጡ ዓመታት ለመጣው ዘላቂ ሰላም፣ የሚታዩና የሚጨበጡ የልማት ስራዎች ፓርቲያቸው አድናቆት እንዳለው አንስተው ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲያቸው የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓርቲው ስም ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የባእድ ተልእኮ በመቀበል ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

እንዲህ አይነት የጥፋት ተልእኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በኦብነግ ውስጥ ምንም አይነት ስፍራ እንደሌላቸው አንስተው በጋራ እንታገላቸዋለን ሲሉም ገልጸዋል።

ኦብነግ በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ በክልሉ ያለውን ጠንካራ የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳየቱን ገልጸው በሰላማዊ ትግል ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት የበኩሉን መወጣቱን ይቀጥላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች በለውጡ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ጥቅምና ለሁለንተናዊ እድገት አጋዥና ደጋፊ በመሆን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም