በክልሉ የግብርና ግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል
ሃዋሳ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የግብርና ግብዓት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በክልሉ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የሲዳማ ክልል የዘንድሮ መኸር እርሻ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት በክልሉ በግብርና ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በተያዘው የመኸር ወቅትም የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
በዚህም የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችል ትርፍ ምርት እንዲመረት አመራሩ ድጋፍና ክትትሉን ማጠናከር አለበት ሲሉም አክለዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ በዘንድሮ የመኸር ወቅት ከ169 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
በምርት ዘመኑ የማሳ ሽፋንን ለማሳደግ እና ምርታማነትን ለሚጨምሩ ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩረት እንደሚሰጥ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።
ለግብርና ሥራው ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መኖሩን አቶ መምሩ ገልጸው፣ በዓመቱ በክልሉ ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን ድረስ ከ75 ከመቶ በላይ የሚሆነውን ለማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በመኸር እርሻው የግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ለውጥ በማምጣት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የዛሬው መድረክ በምርት ዘመኑ ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት አመራሩ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርስ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዱሬሳ ሌዳሞ ናቸው፡፡
በዞኑ በዘንድሮ የመኸር ወቅት ከ43 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል።
ለዚህም የቴክኖሎጂና የግብዓት አጠቃቀም ላይ ለውጥ በማምጣት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡
በንቅናቄ መድረኩ ላይ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ለዘንድሮ የመኸር እርሻ ልማት የተዘጋጁ ሰነዶችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።