ዩኒቨርሲቲው የ''ጀፎረ''ን ማህበረሰባዊ እሴት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የጥናትና ምርምር ሰነድ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የ''ጀፎረ''ን ማህበረሰባዊ እሴት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የጥናትና ምርምር ሰነድ አቀረበ
ወልቂጤ፤ሰኔ 4/2018 (ኢዜአ)፦የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የ''ጀፎረ''ን ማህበረሰባዊ እሴት በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የጥናትና ምርምር ሰነድ ማቅረቡን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የጉራጌ ማህበራዊ እና ባህላዊ መንደር ''ጀፎረ''ን ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ያለውን አበርክቶና በቅርስነት ለማስመዝገብ በሚያስችል የጥናት ሰነድ ላይ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
''ጀፎረ'' በጉራጌ ማህበረሰብ ባህልና አሰፋፈር ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው፣ በየመንደሩ መሃል የሚገኝ ሰፊ፣ ሳር የለበሰ የጋራ አደባባይ ወይም ጎዳና ነው።
ይህ ቦታ ተራ የከተማ መንገድ ሳይሆን፣ በሁለቱም በኩል ያሉ መኖሪያ ቤቶችና የውጪው አጥር የሚገናኙበት የባህል ማዕከል ነው።
''ጀፎረ'' በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለውና በጥንቃቄ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ እንደ ሰብል ማልማት ወይም የግል ህንፃ መገንባት ያሉ ስራዎች ጨርሶ አይፈቀዱበትም።
በአጠቃላይ ጀፎረ የአንድነት፣ የሰላምና የማህበረሰባዊ መስተጋብር ምልክት ሆኖ ያገለግላል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አብድልሙህሲን ሃሰን (ዶ/ር) በውይይቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን እያከናወነ ነው።
የዚሁ አካል የሆነው "ጀፎረ" የዳኝነት እና የእርቅ ስፍራ፣ የበዓላት እና የክዋኔ ማዕከል፣ የምክክርና የደቦ ማህበረሰባዊ እሴትን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን አስረድተዋል።
ጥናታዊ ፅሁፉን ያቀረቡት መምህር መለሰ ሟረታ "ጀፎረ" ከሚሰጠው ማህበረሰባዊ እና ሃገራዊ ጠቀሜታ ባለፈ ለቱሪዝም መዳረሻነት ወሳኝ ቦታ መሆኑን አንስተዋል።
ከጉዳት በመጠበቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተተገበሩ ያሉ ማህበረሰባዊ ደንቦች በአግባቡ እንዲደራጁ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ በበኩላቸው፤ የጀፎረ ማህበረሰባዊ እሴትን ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ቢሮው በጥናት አስደግፎ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ሀገር በቀል እውቀትን ወደ ተግባር በማምጣት የገጠሩ ማህበረሰብን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር ምቹ የቱሪዝም ምህዳር የመፍጠር ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
''ጀፎረ'' ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩበትና የዕርቅ ስርዓት የሚፈፀምበት ስፍራ፣ ጽዳቱ የተጠበቀና የዘመናዊ አኗኗር እሳቤ ማሳያ ነው ያሉት የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ ናቸው፡፡
ከዚህም ባለፈ ለቱሪዝም መዳረሻ ቦታ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው ማህበረሰባዊ እሴቱን እና ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ ተጠብቆ እንዲቆይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።
የጉራጌ የጆካ ባህላዊ ሸንጎ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ወልዴ በበኩላቸው ''ጀፎረ'' ሁሉም በጋራ የሚገለገልበት፣ ፍትህ የሚሰጥበት፣ ደስታና ሃዘን የመሰሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚከወኑበት፣ አባቶች ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የሚሰጡበት የማህበረሰብ የወል ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይም የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የክልሉና የዞን ባህልና ቱሪዝም ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።